ኢትዮጵያ ዛሬ ሁሉም አፍሪካውያን የሚኮሩባት ሀገር ሆናለች ሲሉ አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር) ገለጹ።
"ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ሁሌም ቤቴ እንዳለሁ ያህል ይሰማኛል" የሚሉት ዶ/ር አኪንውሚ አዴሲና ኢትዮጵያ በ10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለምትገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 80 በመቶ የሚሆነውን ፋይናንስ ለማፈላለግ ኃላፊነት የወሰደው የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ናቸው።
ላለፉት 10 ዓመታት ያገለገሉበትን ኃላፊነት በቀጣዩ ወር ከማስረከባቸው በፊት ትናንት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት ለመፈራረም አዲስ አበባ የተገኙት ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ለምን እንደሚወዷት እና ለምን ብዙዎችን እያስገረመች እንደሆነ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ እየበረርኩ ፃፍኩት ባሉት በዚሁ ንግግራቸው፥ ከዓመታት በፊት አንዳንድ አካላት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆን አይገባትም በማለት ይከራከሩ እንደነበር አንስተው፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ሁሉም አፍሪካውያን የሚኮሩባት ሀገር ሆናለች ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የከተማዋን የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሬ እንድጎበኝ ካደረጉ በኋላ ተመልሰህ ስትመጣ ግን አታገኘውም ይሉኝ ነበር፤ እንዳሉትም እየቆየሁ ስመጣ ከተማዋ በአስገራሚ ሁኔታ እየተለወጠች መሆኑን ማየት ችያለሁ ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮያጵያ ኩታ ገጠም የስንዴ ልማትን በ4 ዓመታት ውስጥ ከ500 ሺህ ሄክታር ወደ 2.2 ሚሊዮን ሄክታር በማድረስ በስንዴ ምርት ራሷን በመቻሏ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ማቆሟን በአድናቆት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን ከጎረቤት ኬንያ ጋር በመሠረት ልማት ለማስተሳሰር በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ የተከናወነ ፕሮጀክት መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በ400 በመቶ እንደሚያሳድገው አክለዋል። ሀገሪቱን ከጅቡቲ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር ለማስተሳሰርም ባንኩ ድጋፍ ማድረጉን ነው የተናገሩት።
በአፍሪካ ሀገራት መካከል የኃይል መሠረተ ልማት ትስስርን ለማጠናከር ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ባንኩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል በውጭ ምንዛሬ በመሸጥ በዓመት 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንድታገኝ አስችሏል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ይህ ሁሉ ሊሳካ የቻለው ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ውጤት ለማምጣት ራዕይ ሰንቆ የሚተጋ ቁርጠኛ መንግሥት እና መሪ በመኖሩ ነው ብለዋል የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር)።
በላሉ ኢታላ
#EBC #EBCdotstream #Ethiopia #AfDB