ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ በአረንጓዴ አሻራ የተያዘውን ግብ በጋራ ለማሳካት በትጋት እንሰራለን ሲሉ የጋምቤላ ክልል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ገልጸዋል፡፡
በክልሉ "ኢምፓወሪንግ ኔክስት ጄኔሬሽን" የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ በጋምቤላ ከተማ በዛሬው ዕለት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውኗል፡፡
በችግኝ ተከላው የተሳተፉ በጎፈቃደኛ ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥ በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመከላከል በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በመሳተፍ ችግኞችን በመትከል ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የተስተካከለ ሥነ ምህዳር እንዲፈጠር በማስቻል ላይ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ በዘርፉ የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት እንደሚሰሩም ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡
የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሩ አስተባባሪና የኢምፖወሪንግ ኔክስት ጀነሬሽን ፕሮጀክት ኃላፊ ወጣት ደግሰው ብርሀኑ፤ በአካባቢ ጥበቃና በተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ላይ ወጣቶችን በንቃት በማሳተፍ በዘርፉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የክልሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አሪያት ኡጁሉ በበኩላቸው ፤ በክልሉ በክረምት የበጎፈቃድ አገልግሎት የችግኝ ተከላን ጨምሮ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የበጎፈቃድ ሥራ ለተወሰኑ አካላት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ፣ ሁሉም አካላት በጎ ፈቃደኝነትን የዘወትር ተግባር አድርገው ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸውም የቢሮ ኃላፊዋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በሚፍታህ አብዱልቃድር