በየዓመቱ ነሐሴ 6 የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የወጣቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አስተዋጾ አጉልቶ ለማሳየት ያለመ ነው።
ዕለቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተከበረውም እ.አ.አ በ2000 ነበር።
እያንዳንዱ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ከዘላቂ ልማት እስከ ዲጂታል እድገት፤ ከማህበራዊ እኩልነት እስከ አየር ንብረት ለውጥ ድረስ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ክስተቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ይከበራል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ደግሞ “የወጣቶች ማህበረሰባዊ ተሳትፎ ለዘላቂ የልማት ግቦች” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።
ሃሳቡም የወጣቶች መሰረታዊ ተሳትፎ ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት እና አካታች ማህበረሰቦችን ለመፍጠር አስፈላጊ ነው የሚል መልዕክት አለው ።
ዓለም አቀፉ የወጣቶች ቀን መከበር ወጣቱን በማብቃት ቀጣይነት ካለው እድገት ጋር የማይነጣጠል ትስስር እንዳለው የሚያሳይ ነው።
ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የለውጥ ፈጣሪ መሃንዲሶች ናቸውና በዛሬው ዕለትም ወጣቶች ከአስተዳደር፣ ከኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ባሕላዊ እሴቶችን ከማጎልበት አንፃር ያላቸው ሚና ይታወሳል።
የዘንድሮው የወጣቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ22ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
በሴራን ታደሰ