Search

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከባኩ ከተማ ልምድ በመቀመር የከተማ እድሳት ሥራዎቹን አጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ማክሰኞ ግንቦት 11, 2018 75

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዘርባጃን ባኩ ከተማ የተደረገውን የልማት ተሞክሮ በመውሰድ፣ ታሪክን እና ቅርሶችን ጠብቆ የማቆየት እንዲሁም ዘመናዊ የኮሪደር ልማትን የማስፋፋት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድኑን የባኩ ጉብኝት መነሻ በማድረግ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት፣ የባኩ ከተማ በጥንታዊ ቅርሶች አያያዝ እና በከተማ እድሳት ያሳየችውን ስኬታማ ተሞክሮ አድንቀዋል። 

በተለይምባኩ - ጥንታዊቷ ከተማ" በሚል የሚታወቀውን ታሪካዊ ስፍራ በጥንቃቄ በማደስ ለቱሪዝም ክፍት ማድረጓን፣ እንዲሁም ቀደም ሲል "ጥቁሯ ከተማ" ይባል የነበረን ጎስቋላ ስፍራ በማፍረስ "ነጭ ከተማ" በተሰኘ ውብ እና ዘመናዊ መልክ መገንባቷን እንደ አርአያነት አንሥተዋል።

ይህ የከተማ እድሳት ሂደት የአዲስ አበባን እና የኢትዮጵያን ተሞክሮ የሚያንፀባርቅ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ በኢትዮጵያም ታሪክን እና ቅርሶችን በመጠበቅ እንዲሁም ጎስቋላ አካባቢዎችን በአዲስ መልክ በመገንባት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በዚህም በቅርስ ጥበቃ ረገድ፦ በፒያሳ እና በአራት ኪሎ አካባቢ የሚገኙ ጥንታዊ ሕንፃዎችን፣ የመጀመሪያውን ሲኒማ ቤት፣ ማዘጋጃ ቤቱን፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን እና የተለያዩ ሐውልቶችን በማደስ ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም እንደ ሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጎንደር ፋሲል ቤተ መንግሥት ያሉ ታላላቅ ቅርሶች መጠገን እና መታደስ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በኮሪደር ልማት፦ ጎስቋላ እና ለመኖር ምቹ ያልነበሩ አካባቢዎችን በማፍረስ፣ በምትኩ ዘመናዊ እና ምቹ የመኖሪያ እና የሥራ ቦታዎችን የመገንባት ሥራ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። 

በቅርቡ በመዲናዋ የተተገበረው ሰፊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ለዚህ ዋና ማሳያ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ከተማዋን ለእግረኛ እና ለብስክሌት ምቹ፣ አረንጓዴ እና ዘመናዊ ከማድረጉም ባሻገር የመንገድ መሠረተ ልማትን በማዘመን የከተማዋን ገጽታ በአበረታች ሁኔታ እንደቀየረው አስታውቀዋል።

የባኩ ጉብኝት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የተጀመሩትን የከተማ ልማት፣ የቅርስ ጥበቃ እና ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል ትልቅ ልምድ የተቀሰመበት አጋጣሚ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አረጋግጠዋል።

#EBC #Ethiopia #addisababa #corridordevelopment #city #rejuvenation

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ:

ተያያዥ ዜናዎች: