በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ዲጂታል ሥርዓት እየተቀየረች ነው፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ታሪካዊ ጉዞ አካል ሆናለች።
በዚህ የሽግግር ወቅት የሀገራትን መፃኢ ዕድል፣ ምጣኔ-ሀብታዊ ዕድገት እና ብሔራዊ ደኅንነት የሚወሰነው በቴክኖሎጂ ልማት ብቻ ሳይሆን የመረጃ ሉዓላዊነትን በተሟላ መልኩ በማረጋገጥ ጭምር ነው።
የመረጃ ሉዓላዊነት ማለት በአንድ ሀገር ውስጥ የሚመነጩ፣ የሚሰበሰቡ እና ጥቅም ላይ የሚውሉ መረጃዎች በሀገሪቱ ሕግ እና ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ የማድረግ መብት እና አቅም ነው።
ይህ ጽንሰ-ሀሳብ ለኢትዮጵያ የሀገር እና መንግሥት ግንባታ ሂደት ያለው አስተዋጽኦ ዘርፈ-ብዙ እና ወሳኝ ነው።
የመረጃ ሉዓላዊነት መረጋገጡ ሀገር ለሳይበር ጥቃቶች እና ለሳይበር ሰላዮች የመጋለጥ ዕድሏን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል።
በተጨማሪም የመረጃ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ለሀገር በቀል ምጣኔ-ሀብት ዕድገት የላቀ አንድምታ አለው።
ሀገር የመረጃ ሉዓላዊነቷን ስታረጋግጥ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ተቋማት እና የፈጠራ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች መረጃዎችን መሠረት ያደረጉ መተግበሪያዎችን እና አገልግሎቶችን እንዲያበለጽጉ ሰፊ ዕድል ይፈጥርላቸዋል።
የሀገር ውስጥ መረጃዎችን በውጭ ሀገራት የክላውድ (Cloud) አገልግሎት ላይ ለማስቀመጥ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ለሌሎች የልማት ሥራዎች ማዋል ይቻላል።
ከዚህም ባሻገር የመረጃ ደኅንነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ከመረጃ ምዝበራ የመታደግ አቅም ከመፍጠሩም በላይ የመረጃን ተአማኒነት ደረጃንም ከፍ ያደርጋል።
ይህ ደግሞ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን እምነት በማጠናከር ረገድ ለሀገር ግንባታ ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የጀመረችውን የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ የመረጃ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ምርጫ የሌለው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ተመልክቷል።
በሀና ምንዳሁን