Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከውስጥ አቅምና ከታሪካዊ ፍትህ አንጻር ሲቃኝ

ማክሰኞ ግንቦት 11, 2018 158

ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የባሕር በር መብታችን ከቅንጦት ባለፈ፣ የህልውናችንና የብልጽግናችን ማረጋገጫ ሆኖ በብሔራዊ አጀንዳነት ቀዳሚውን ቦታ ይዟል። አዲሱ ትውልድ በየመስኩ እያስመዘገበ ያለው ድንቅ ውጤት፣ ኢትዮጵያ ለዘመናት የኖረችበትን የየብስ እግረ-ሙቅ የምትበጥስበት ጊዜ መቃረቡን በጉልህ እያሳየ ነው። ይህ ትውልድ በታላላቅ ፕሮጀክቶች፣ በግብርናው አብዮትና በዘመናዊ የኢኮኖሚ መዋቅሮች የገነባው አቅም፣ የባሕር በርን የማግኘት ህልማችንን ከፍላጎትነት ወደ ተጨባጭ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድርድር ከፍታ አሸጋግሮታል።  

የባሕር በር ለኢትዮጵያ እንደ ሰው ሳንባ ነው፤ ሳንባው የታፈነ ሰው ደግሞ በረጅም ሩጫ ተወዳድሮ ሊያሸንፍ አይችልም። ዛሬ በየገበያው የምናየው የሸቀጦች ዋጋ መናር፣ የሎጂስቲክስ መጓተትና የኑሮ ውድነት ሰንሰለቱ ሲመረመር መጨረሻው የሚገናኘው ወደብ አልባ ከመሆናችን ጋር ነው። ይህ ትውልድ ይህንን እውነታ ተረድቶ፣ የባሕር በርን የማግኘት ጥያቄ እንደ ታሪካዊ መብትና ኢኮኖሚያዊ አስፈላጊነት በዓለም አቀፍ መድረክ እያቀረበ ይገኛል።

የዚህ ጥረት ዋነኛ ማሳያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው። ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያውያን የልማት አቅም መገለጫ ብቻ ሳይሆን፣ የዲፕሎማሲያችንም ኃይል ነው። ግድቡ ለቀጣናው ሀገራት የምናቀርበው የንጹህ ኃይል ምንጭ በመሆኑ፣ ለባሕር በር ጥያቄያችን ትልቅ መነሻ ሆኗል። የባሕር በርን ለማግኘት ስንደራደር፣ ግድቡ የሚሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል እንደ ድርድር መሣሪያ ሆኖ ማገልገሉ፣ የኢትዮጵያን የድርድር አቅም ከየትኛውም ጊዜ በላይ ከፍ አድርጎታል። 

በሌላ በኩል፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ የታየው ስኬት የኢኮኖሚ ጥንካሬያችን ሌላው ማሳያ ነው። የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተከናወነው የስንዴ ልማት አብዮት፣ ኢትዮጵያ ከምግብ እርዳታ ወደ ምርት ላኪነት እየተሸጋገረች ነው። በዘመናዊ የመስኖ ቴክኖሎጂ የታጀበው ይህ የምርት ጥራት፣ ለኢትዮጵያ ምርቶች ዓለም አቀፍ ገበያን የመወዳደር አቅም ፈጥሯል። ይህ የግብርና ምርታማነት፣ የባሕር በር ባለቤት ስንሆን ምርቶቻችንን በቀጥታ ወደ ዓለም ገበያ ለማውጣት የምንጠቀምበት ጉልበት ነው። የኢኮኖሚ መሠረታችን በጠነከረ ቁጥር፣ የባሕር በር ጥያቄያችንም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እያገኘ ይሄዳል።

አዲሱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በትራንስፖርትና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ያስመዘገባቸው ድሎች፣ ኢትዮጵያ ከአንድ ወደብ በላይ እንድታስተናግድ የሚያስችል ስልታዊ አቅም እንዳላት እያረጋገጡ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለምን ሰማይ የገዛበትና በአፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል የሆነበት መንገድ፣ የንግድ አቅማችንን ከባሕር በሮች ጋር ለማስተሳሰር ትልቅ መንገድ ጠቋሚ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ወደ ምርት መሸጋገራቸውና የወደብ መውጫ ፍላጎታችን መጨመሩ፣ የባሕር በርን አስፈላጊነት ከምንጊዜውም በላይ አሳማኝ አድርጎታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በምታስመዘግበው የላቀ የኢኮኖሚ እድገት፣ የባሕር በርን ማግኘቷ ለጎረቤት ሀገራትም ቢሆን ተጨማሪ የኢኮኖሚ ዕድልና የቀጣናዊ ትስስር ዋስትና የሚሰጥ ነው።

በአጭሩ፣ አዲሱ ትውልድ በአጭር ጊዜ የገነባው የኢኮኖሚ መዋቅርና የዲፕሎማሲ ጥንካሬ፣ ለባሕር በር ጥያቄያችን የሚያስፈልገውን መንገድ እየጠረገ ይገኛል። የህዳሴው ግድብ ኃይልና የግብርናው ምርታማነት፣ የባሕር በር ፍላጎታችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ በክብርና በኩራት እንድንጠይቅ የሚያስችለን የኢኮኖሚ መሰረት ናቸው። ኢትዮጵያ የባሕር በርን ስታገኝ፣ ለቀጣናው የምታበረክተው አስተዋፅኦ ለጎረቤቶቿም የጋራ ጥቅም የሚሆንበትን መንገድ ይህ ትውልድ ይከፍታል።

ይህ ትውልድ የታሪክ እዳውን በመክፈል፣ የባሕር በርን ማግኘቱን የዚህ ትውልድ የድል አክሊል እንደሚያደርገው ምንም ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ስታገኝ፣ የዚህ ትውልድ ድንቅ ተግባራት ታላቅነታቸው በዓለም አቀፍ ውቅያኖሶች ላይ ይውለበለባል። የባሕር በር ጥያቄ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳ በመሆኑ፣ 2018 . የኢትዮጵያ የልማት ምዕራፍ፣ ይህ ህልም እውን የሚሆንበት ጉዞ በድል መጠናቀቁ አይቀርም። 

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ