የሀገርን የውስጥ ፖለቲካዊ ፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎችን ማመንጨት፡ በራስ አቅም መቃኘት፣ በጥንቃቄ ማደራጀትና ለስትራቴጂካዊ ውሳኔዎች ማዋል መቻል “የመረጃ ባለቤትነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት” ተብሎ ይበየናል።
መረጃ የፖሊሲዎች ሁሉ መነሻ፣ የዕቅዶች ሁሉ መሠረት እና የሀገርን የነገ አቅጣጫ አመላካች በመሆኑ በባለቤትነት መያዝ የነፃነት ሁሉ ጥግ ነው። ኢትዮጵያ ለአሥርት ዓመታት ስለ ዜጎቿ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መረጃ ለማግኘት በውጭ ተቋማት ትንበያ ላይ ጥገኛ የነበረች ቢሆንም አሁን ላይ ይህን ታሪክ በመቀየር የራሷን መረጃ በራሷ ባለሙያዎች የማመንጨትና የማስተዳደር ሙሉ ብቃት ላይ ደርሳለች።
ይህ ሽግግር “የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በተከበረው የአፍሪካ ስታትስቲክስ ቀን እና በተካሄደው ጉባኤ ላይ በጉልህ ተንጸባርቋል። የዳታ አብዮት እና የዲጂታል ዘመናዊነት ሥራዎች ኢትዮጵያ ከውጭ አካላትና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የመረጃ ጥገኝነት ፍፁም ለመውጣት የሚያስችል፣ ስልታዊና መዋቅራዊ ይዘት ያለው የሦስት ዓመት የብሔራዊ ስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም (NSDS) ቀርጻ በስፋትና በጥልቀት እየተገበረች ትገኛለች። ይህ መርሃ-ግብር ተራ የቁጥሮች ስብስብ ሳይሆን የኢትዮጵያን የነገ ዕጣ ፈንታ በራስ እውነታ ላይ ለመወሰን የተነደፈ የዳታ አብዮት ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በሰፊው እንደሚገልጹት ቀደም ሲል የሀገራችንን መረጃዎች በማመንጨት፣ በማደራጀትና በመተንተን ረገድ የነበረውን የውጭ አካላት ተጽዕኖና የተዛባ ፍርድ በማስቀረት፣ በራስ አቅም ጥራት ያለውና አስተማማኝ መረጃን የማልማት ሥራ አሁን ላይ በልዩ ትኩረትና ቁርጠኝነት ተጀምሯል። ለዘመናት የውጭ ተቋማት የራሳቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች መሠረት በማድረግ የሚሰጡት ግምትና ትንበያ የኢትዮጵያን ዕቅዶች ሲያወናብድ የነበረበት የታሪክ ጠባሳ አሁን በሀገር በቀል ባለሙያዎችና በዘመናዊ የዲጂታል መሠረተ-ልማቶች ሙሉ በሙሉ እየተቀየረ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተከናወነውና መጠናቀቁ የተበሰረው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ የልማትና የኢኮኖሚ ድርጅቶች መኖራቸውን በይፋ አረጋግጧል። ይህ ግዙፍ የዳታ ማዕከል ለከተማ ልማት፣ ለንግድ ስትራቴጂዎችና ለማክሮ-ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንደ ዋነኛ የቁጥር ጋሻ ሆኖ ያገለግላል። ከ23 ዓመታት ረጅም መቆራረጥ በኋላ እስከ ወረዳ ደረጃ ድረስ የዘለቀ ሰፊና ውስብስብ የግብርና ምርት ቆጠራም ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መንገድ ተከናውኗል። የዚህ ቆጠራ ልዩ ባህሪ 92 በመቶው መረጃ በአካልና በዘመናዊ ታብሌቶች (Tablets) የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው 8 በመቶው ደግሞ በከፍተኛ የሪሞት ሴንሲንግ (Remote Sensing) እና የሳተላይት ቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ ነው።
ይህም የመረጃውን ትክክለኛነት፣ ጥራትና ተዓማኒነት ወደ ላቀ ዓለም አቀፍ ደረጃ አሳድጎታል። የሀገር መረጃ የሀገር ደህንነት በመሆኑ፣ የዳታ አያያዙና ጥበቃው በቨርችዋል ዴስክቶፕ ኢንፍራስትራክቸር (Virtual DesktopInfrastructure) ሥርዓት እንዲመራ ተደርጓል። ይህ ቴክኖሎጂ ሀገራዊ መረጃዎች እንዳይሰረቁ፣ እንዳይበረዙ ወይም ያለፈቃድ ለውጭ አካላት እንዳይጋለጡ አስተማማኝ ከለላ በመሆን የመረጃ ሉዓላዊነትን በተግባር አረጋግጧል።
አንድ ዕቅድ፣ አንድ ሪፖርት፣ አንድ በጀት የመረጃ ሉዓላዊነትን የማረጋገጡ ጉዞ ሌላው መገለጫ ያልተቀናጀ የመረጃ ሥርዓትን በመውጣት፤ ወደተቀናጀ ዲጂታል እና ወደ ሀገር በቀል የመረጃ ሥነ ምህዳር መሸጋገር መቻሉ ነው። "አንድ ዕቅድ፣ አንድ ሪፖርት፣ አንድ በጀት" የሚለውን የተቀናጀ ሀገራዊ አሠራር በተቋማት መካከል ሙሉ በሙሉ ለማስፈን እየተሰራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሀገራችን ለጀመረቻቸው የሪፎርም ሥራዎች የሚያግዙ መረጃዎችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች እያቀበለ ይገኛል።
ይህም መንግስት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ቀረጻ እና ውሳኔ አሰጣጥ እንዲከተል በማድረግ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ እና ደህናነት ለማረጋገጥ መሠረት ጥሏል። ከመረጃ ሉዓላዊነት እስከ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ይህ የስታትስቲክስ ዘርፍ ማሻሻያ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በሀገራችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጨባጭ ለዉጥ እያመጣ ይገኛል። አስተማማኝ መረጃን መሠረት በማድረግ በተወሰዱ እርምጃዎች የሚከተሉት ስኬቶች ተመዝግበዋል፦ የዘርፍ ትራንስፎርሜሽን፡ የማምረቻ ኢንዱስትሪው የገበያ ድርሻ ከ25 ወደ 46 በመቶ ከፍ እንዲል፣ የወርቅ ኤክስፖርት እንዲያድግና የ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ ተደራሽነት እንዲሰፋ በማድረግ ረገድ መረጃን መሠረት ያደረገው አሠራር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
አህጉራዊ ሚና እና የወደፊት ተስፋ ኢትዮጵያ የስታቲስቲክስ ሉዓላዊነቷን በማረጋገጥ ዕጣ ፈንታዋን በገዛ አቅሟ እየወሰነች መሆኗ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአህጉር ደረጃም ትልቅ ትርጉም አለው። ዘንድሮ የአፍሪካ ስታትስቲክስ ቀን "የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ትግበራን ለማፋጠን የመረጃ ሥነ-ምህዳሮችን ማዘመን" በሚል መሪ ቃል መከበሩ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት እውን እንዲሆን ከፈረሙ አገራት የመጀመሪያዋና ትግበራውን ለማፋጠን በባለቤትነት የያዘች አገር በመሆኗ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓቷ ለአህጉራዊ ኢኮኖሚ ውህደትም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ምንም እንኳ ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ተጽዕኖ ቢኖራቸውም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ውጤት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚውን መሠረት የማስፋፋት ሥራ እና የዲፕሎማሲው መስክ ስኬቶች ወደ ላቀ የብልጽግና ምዕራፍ እየተሻገረች መሆኑን የሚያሳዩ የማይካዱ እውነታዎች ናቸው። የስታቲስቲክስ ሉዓላዊነት ደግሞ ለዚህ ጉዞ አስተማማኝ ኮምፓስ ሆኖ ያገለግላል።
ሁለንተናዊ ፋይዳ እና ስትራቴጂካዊ ውጤቶች የመረጃ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ በቀላሉ ደረቅ የቁጥሮች ስብስብ ከመያዝ ባሻገር የአንድን ሀገር የኢኮኖሚ ነፃነት የመጠበቅና የመከላከል የደህንነት ጋሻ ነው። ራሱን በራሱ የሚያውቅ፣ የውስጥ አቅሙንና ውስንነቱን በትክክል የሚገነዘብ ማኅበረሰብ የመገንቢያ መሠረት ነው። የዚህ ታላቅ የዳታ አብዮት ዋነኛው ስልታዊ ፋይዳ የውጭ ተፅዕኖዎችን እና የተዛቡ ፍርዶችን ማስቀረት መቻሉ ነው። የራስን መረጃ በራስ አቅም ማመንጨት፣ የውጭ ድጋፍ ሰጪዎችና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የራሳቸውን ፖለቲካዊ አጀንዳ፣ መመዘኛና ከሀገራችን ተጨባጭ እውነታ የራቁ ትንበያዎችን እንዳይጭኑብን ትልቅ ከለላ ሆኖ ያገለግላል።
ሀገር የራሷን መስታወት በራሷ ስትሰራ፣ ሌላው የሚሰጣትን የተሰበረ መነጽር ማውለቅ ትችላለች። ይህ ሽግግር የሀገሪቱን ውስን ሀብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የሀብት አጠቃቀም ውጤታማነትን ያረጋግጣል። በትክክለኛና በተረጋገጠ ቁጥር ላይ የተመሠረተ ዕቅድ ማውጣት መቻሉ፣ ሀገራዊ በጀትንና የልማት ሀብትን በትክክለኛው ቦታ፣ ለትክክለኛው ማኅበራዊ ክፍተትና ፕሮጀክት ሳያባክኑ በጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል።
ይህም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ግልጽነትን ከመፍጠሩ ባለፈ፣ በቁጥር ላይ የተመሠረተ ተጠያቂነት በየደረጃው እንዲሰፍን ያደርጋል። በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ዳታ ከዓለም አቀፍ ትንበያ ጋር ያለው ልዩነት ከአንድ በመቶ በታች መሆኑ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድና የፋይናንስ መድረክ ላይ ያላትን ተዓማኒነት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምረዋል። ይህ ተዓማኒነት ደግሞ ዘላቂና አስተማማኝ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደ ትልቅ ማረጋገጫ ሆኖ ያገለግላል።
የፖሊሲ አቅጣጫ እና የሪፎርምቅኝት ከፖሊሲ አንጻር ሲታይ የስታቲስቲክስ ሉዓላዊነት በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ቀረጻ ሥርዓትን ወደ ፍፁም የብስለት ምዕራፍ አሸጋግሮታል። ቀደም ሲል የነበሩ መዋቅራዊ ድክመቶችን በመቅረፍ፣ ፖሊሲዎች ከላይ ወደ ታች በግምትና በፖለቲካዊ ፍላጎት ብቻ የሚወርዱ ሳይሆን ከታች ከወረዳና ከኢኮኖሚ ድርጅቶች በተሰበሰበ ግልጽ መረጃ ላይ ተመስርተው እንዲቀረጹ አድርጓል።
ይህ መሬት የረገጠ አሠራር የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች በተሳካ ሁኔታ እንዲመሩ፣ የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ እርምጃዎች የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በሳይንሳዊ መንገድ እንዲቀየሱ እና የመንግሥት የድጎማ ሥርዓት በትክክል የታለመውን የኅበረተሰብ ክፍል እንዲደግፍ ስልታዊ አቅጣጫ አስይዟል።
መረጃ የፖሊሲዎች ጋሻና መሪ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያን የፖሊሲ ነፃነት በተግባር አረጋግጧል። በውጭ ተቋማት የተሳሳቱ የቁጥር ትንበያዎች ሳቢያ ይወሰዱ የነበሩ የተሳሳቱ የፖሊሲ ማስተካከያዎች ተቀርፈው፣ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕጣ ፈንታ በራሷ እውነታ ላይ ብቻ እንዲወሰን ሆኗል። ይህም መንግስት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን ሲነድፍ የውስጥ አቅሙን መሠረት አድርጎ እንዲንቀሳቀስና የውጭ ጫናዎችን የመቋቋም አቅሙን እንዲያሳድግ አስችሎታል።
የወደፊት የቤት ሥራዎች እና መደረግ ያለባቸው ተግባራት የተጀመረው ታሪካዊ ሽግግር ዘላቂ መሠረት እንዲኖረውና ወደ ብልጽግና ለመሻገር በቀጣይነት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አበይት ተግባራት አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የጀመረውን የዲጂታል አብዮት በማስቀጠል፣ የሰው ሠራሽ አስተዋፅኦ እና የቢግ ዳታ ትንተና ዘዴዎችን በስታቲስቲክስ አገልግሎት ውስጥ በስፋት ማላመድና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል። ዓለም
በየሴኮንዱ የመረጃ ማዕበል የምታመርትበት ዘመን ላይ በመሆኗ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ሥርዓትም ይህንን ፍጥነት መከተልና የጀመራቸዉን የቀጥታ መረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችን ማጎልበት አለበት።
እንዲሁም አንድ ዕቅድ፣ አንድ ሪፖርት፣ አንድ በጀት የሚለውን መርህ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በሁሉም የመንግሥትና የግል ተቋማት መካከል ያለው የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ያለምንም መቆራረጥ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መረብ እንዲገናኝ ማድረግ ነው።
የተበታተኑ የመረጃ ቋቶች ተሰባስበው በአንድ ማዕከላዊ ሥርዓት ውስጥ ሲቀናጁ የሀገር መሪዎች ፈጣንና ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመስጠት አይቸገሩም። በተጨማሪም በዳታ ሳይንስ፣ በሪሞት ሴንሲንግ እና በከፍተኛ የኢኮኖሚ ሞዴሊንግ ዙሪያ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም በየደረጃው መገንባትና ማብቃት እጅግ ወሳኝ ተግባር ነው። ቴክኖሎጂው የሚመራው በሰለጠነ የሰው ኃይል በመሆኑ፣ የዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ትስስር ከስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር ሊጠናከር ይገባል።
በመጨረሻም፣ ከመንግሥት መዋቅር ባለፈ፣ በሕዝብ፣ በምርምር ተቋማትና በግሉ ዘርፍ መረጃን ለውሳኔና ለፈጠራ ሥራዎች የመጠቀም ባህልን ማጠናከር ያስፈልጋል። መረጃ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የዜጎችም መሪ መሆን ሲችል ነው የዳታ አብዮቱ ፍሬ ማፍራት የሚችለው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የመረጃ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞ የነፃነትና የብልጽግና አዲስ ምዕራፍ ነው። ምንም እንኳ ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ተጽዕኖዎች ቢኖሩም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ውጤት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚውን መሠረት የማስፋፋት ሥራ እና የዲፕሎማሲው መስክ ስኬቶች ወደ ላቀ የብልጽግና ምዕራፍ እየተሻገረች መሆኑን የሚያሳዩ የማይካዱ እውነታዎች ናቸው።
የስታቲስቲክስ ሉዓላዊነት ደግሞ ለዚህ ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ሽግግርና ጉዞ ፍፁም አስተማማኝ ኮምፓስ ሆኖ ያገለግላል። ሀገራችን በገዛ እውነታዋ ላይ ተመስርታ የራሷን ዕጣ ፈንታ በራሷ የመወሰን ጽኑ መሠረት ጥላለች፤ ይህንንም ይበልጥ በማጠናከር የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሁላችንም የጋራ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
በረከት ሽመልስ