በአፋር ክልል ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት አደጋን ለመከላከል እና ጉዳትን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።
በቅርቡ በላይኛው አዋሽ ከባድ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን ተከትሎ በመካከለኛው እና በታችኛው አዋሽ ሊያጋጥም የሚችለውን አደጋ ለመከላከል እና ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ እየተከናወኑ መሆኑን ነው ዋና ኮሚሽነር መሐመድ ሁሴን የተናገሩት።
በክልሉ የጎርፍ መከላከል ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል ካልሆነም ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ዋና ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።
በክልሉ የዝናብ መጠኑ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በመካከለኛው እና በታችኛው አዋሽ የጎርፍ ስጋት ያለባቸው 13 ወረዳዎች እና 62 ቀበሌዎች ተለይተው የቅድመ ጥንቃቄ መልዕቶችን ከማስተላለፍ ጀምሮ ነዋሪዎችን ወደ ከፍታ ቦታዎች የማዛወር ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ትናንት በአፋምቦ ወረዳ የጣለው ከባድ ዝናብ በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን ማፈናቀሉን የገለፁት አቶ መሐመድ፤ ነዋሪዎችን ወደ ከፍታ ቦታ የማዛወር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል በአፍዴራ እና ዳሎል በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች ክልሉ በራስ አቅም አስቸኳይ እርዳታ የማቅረብ ሥራ ማከናወኑን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በክልሉ የአደጋ ስጋት መጨመሩን ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ከሌሎች አካላት ከሚያገኛቸው ድጋፎች በተጨማሪ ተጠባባቂ በጀት በመመደብ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
በሁሴን መሐመድ
#EBC #EBCdotstream #Afar #floodprevention