Search

ሀሰተኛ መረጃን ለመመከት መደበኛ ሚዲያዎች ያላቸው ሚና

ማክሰኞ ነሐሴ 06, 2017 107

በማህበራዊ የትስስር ገፆች እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች አላማቸው ቢለያይም የየራሳቸውን ጉዳት ማድረሳቸው አይቀርም ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

እነዚህን ጉዳት የሚያደርሱ ሀሰተኛ መረጃዎችን የመከላከል ተግባሩ የእያንዳንዱ ዜጋ ቢሆንም እውነታን በማሳየት ረገድ ደግሞ መደበኛ ሚዲያዎች የሚጠበቅባቸው ሚና የጎላ እንደሆነ ይገለጻል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ መደበኛ ሚዲያዎች ተዐማኒነታቸው ሲጨምር እና መረጃን በፍጥነት ባደረሱ ቁጥር የሀሰት መረጃዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ ሲሉ ይገልጻሉ።

የሀሰት መረጃ የሚነሳው ከመንደር አሊያም ከማህበረሰቡ ውስጥ ቢሆንም እየሰፋ እና ብዙዎች ዘንድ ሲደርስ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ይህን ለመከላከልም እውነትን ያላቸውን መረጃዎች ለሕዝብ በማድረስ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

በዋነኝነት በፌደራል ደረጃ የሀሰት መረጃዎችን ለመቆጣጠር በይበልጥ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ማህበረሰቡ የሀሰት መረጃዎች ላይ እንዳያተኩር በቂ መረጃን ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው መሆኑም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።

የሀሰት መረጃዎችን ከመከላከል አንፃር መደበኛ ሚዲያዎች በቀጣይም ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ መረጃዎችን ወቅቱን ጠብቀው የማቅረብ እና በቂ መረጃን ለሕዝቡ የማድረስ ኃላፊነታቸውን በላቀ ሁኔታ ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።



በሄለን ተስፋዬ


#EBC #ebcdotstream #FactCheck