Search

ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 2 ሚሊዮን ቶን ሰብል ለማምረት እየሰራች ነው ፦ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

Aug 12, 2025

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍን በእራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ሥራዎች እያከናወነች መሆኑን በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል።  

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና መረጃ ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፍራኦል በቀለ (ዶ/ር) ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ወቅታዊ ውይይት ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ዘላቂ እና አስተማማኝ የሰብዓዊ ድጋፍ ክምችት ላይ እየሰራች ነው ብለዋል።

የሌሎች ተመፅዋች የሆነ ሀገር ለተለያዩ ተፅዕኖዎች ተጋላጭ ነው ያሉት ዶክተር ፍራኦል፤   በፈንድ  አቅረቦት፣ በምርት ክምችት እና በመጋዘን ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በ2016 ዓ.ም በተጀመረው የምርት ሥራ 253 ሺህ ሔክታር መሬት መልማቱን እና ለሰብአዊ ድጋፍ ብቻ የሚውል 2 ሚሊዮን ቶን ሰብል ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ለአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ የሚውል ሲሆን፤ ቀሪው 500 ሺህ ቶን በብሔራዊ ክምችት መጋዘን የሚቀመጥ ነው ብለዋል።  

ሁሉም ክልሎች የሚጠበቅባቸው የምርት መጠን ሥራ የተሰጣቸው መሆኑን ጠቁመው፤  ምርት የማያቀርቡ ክልሎች ወይም ከተማ አስተዳደሮች ደግሞ ከዓመታዊ በጀታቸው ላይ የምርት ግዢ እንዲፈፅሙ አቅጣጫ መቀመጡን አመላክተዋል።

 

በቤተልሔም ገረመው