Search

ሰላም ቅርሶቿን ያስመለሰላት ጥንታዊቷ የማሊ ከተማ - ቲምቡክቱ

Aug 12, 2025

የማሊዋ ጥንታዊቷ ከተማ ቲምቡክቱ ከኒጀር ወንዝ በስተሰሜን 20 ኪሎ ሜትር ርቃ ትገኛለች።

ከተማዋ ከማሊ ስምንቱ የአስተዳደር ክልሎች አንዷ ስትሆን የቶምቡክቱ አውራጃ ዋና ከተማም ነች።

የአርኪዎሎጂ ግኝቶች እንደሚያመላክቱት በመካከለኛው ዘመን ከተማዋ የእስልምና ትምህርት እና ንግድ ታዋቂ ማዕከል ሆና አገልግላለች።

ቲምቡክቱ እንደ ጊዜያዊ ማራፊያ ሆና ብትቆረቆርም በ12ኛው ክፍለ ዘመን ቋሚ ከተማ ሆና ማገልገሏን ታሪኳ ያስረዳል።  

በተለይም እ.ኤ.አ 1325 አካባቢ ማንሳ ሙሳ የተሰኘው ንጉስ ከጎበኛት በኋላ ቲምቡክቱ በስትራቴጂካዊ አቀማመጧ ምክንያት፣ የጨው፣ የወርቅ እና የዝሆን ጥርስ ንግድ ማዕከልም ሆና ነበር።

በ14ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የማሊ ስርወ መንግሥት አካል ከመሆኗ በፊት ታዋቂ የእስላምና ትምህርት ማዕከል ሆና በርካታ ምሁራንንም ስባለች።

ታዲያ ይህች ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከተማ ፥ ከ13 ዓመታት በፊት ከአሸባሪው አልቃይዳ ቡድን ጋር ግንኙነት ባላቸው ታጣቂዎች ተይዛ ነበር።

 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያዎች እንዳሉት አሸባሪዎቹ እ.ኤ.አ. በ2012 ቲምቡክቱን ከያዙ በኋላ ከ4ሺህ በላይ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን አውድመዋል።

አንዳንዶቹ ጽሑፎች በ13 ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉም ነበሩ። ከዚህ ባለፈ አሸባሪዎቹ ዘጠኝ ጥንታዊ የመቃብር ቦታዎችን እና መስጂዶችን አውደመዋል።

ከ13 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከነበሩት ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል ከ27 ሺህ በላይ የሚሆኑት እንዳይወድሙ ለመከላከል፤ ከተቀመጡበት የቲምቡክቱ ቤተ-መጽሐፍት በሩዝ ከረጢቶች፣ በጋሪ፣ በሞተር ሳይክል፣ በጀልባ እና በተሽከርካሪዎች አሸባሪዎቹ ወደማያገኟቸው ወደሌላ አካባቢዎችም ተወስደው ነበር።

አሁን ላይ በከተማዋ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ የማሊ ወታደራዊ መንግስት ከ12 ዓመታት በፊት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ባላቸው አሸባሪዎች በተያዘችበት ወቅት ከቲምቡክቱ ወደሌሎች አካባቢዎች ተወስደው የነበሩ ታሪካዊ የእጅ ጽሑፎችን ወደ ከተማዋ መመለስ ጀምሯል።

የቲምቡክቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ዲያሃራ ቱሬ፥ "ጥንታዊ ጽሑፎቹ ሥልጣኔያችንን፣ መንፈሳዊ እና ትምህርታዊ ቅርሶቻችንን ስለሚያንፀባርቁ መመለሳቸው ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ደስታን የፈጠረ ነው" ብለዋል።

ዩኔስኮ የዓለም የባህል ቅርስ አካል አድርጎ የሰየማቸው ጥንታዊ ጽሑፎቹ፣ ከእስልምና ትምህርት፣ ከሕግ ትምህርት፣ ከሥነ ፈለክ ጥናት፣ ከሕክምና፣ ከሒሳብ፣ ከታሪክ እና ከጂኦግራፊ የተውጣጡ በርካታ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን የያዙ ናቸው።

ጥንታዊ ጽሑፎቹ ከዚህ ባለፈም በምዕራብ አፍሪካ ለሚገኙት የማሊ እና የሶንግሃይ ስርወ መንግሥት የበለጸጉ የባህል ቅርሶች ምስክር ናቸው።

ማሊ ከአጎራባቾቿ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ጋር በመሆን ከአልቃይዳ እና ከእስላማዊ መንግስት ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ታጣቂዎችን ስትዋጋ መቆየቷ ይታወሳል።

 

 

በሰለሞን ከበደ