Search

የአረንጓዴ ዐሻራ ፍሬያቸውን የቀመሱት የአዳማ አርሶ አደሮች

Aug 12, 2025

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ምርት መስጠት በመጀመራቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን በአዳማ ከተማ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም የተከሏቸው የፓፓያ፣ የቮካዶ፣ የሙዝ እና የብርቱካን ችግኞች በቂ እንክብካቤ በማግኘታቸው አሁን ላይ ምርት መስጠት መጀመራቸውን በአዳማ ከተማ በደምበላ ክፍለ ከተማ የሚገኙት አርሶ አደሮች ለኢቢሲ ገልጸዋል።  

ምርቱንም ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን  ነው የተናገሩት።

 

 

በ2015 የተተከለው የፓፓያ ችግኝ ከ9 ወራት በኋላ ምርት መስጠት በመቻሉ እስካሁን ሁለት ጊዜ ምርት ማግኘታቸውንም ነው አርሶ አደሮቹ ያስረዱት፡፡ 

በከተማዋ በአረንጓዴ አሻራ ለምግብነት የሚያገለግሉ የፍራፍሬ ችግኞች ከተተከሉ በኋላ በአጭር ጊዜ ምርት በመስጠታቸው ለሸማቾችም ሆነ ለተጠቃሚዎች  ከፍተኛ ጥቅም አስገኝተዋል ይላሉ አርሶ አደሮቹ፡

ላለፉት 7 ዓመታት እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ብዝሃ ሕይወት ጥበቃን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲቲዩት ተባባሪ ተመራማሪ ሻምበል ቀነኒሳ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡

በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ የሚስከትለውን ጉዳት በመቀነስ፤ የውሃና የአፈር ጥበቃን በማሻሻል፤ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ እንዲሁም የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ውጤት ማስመዝገቡን አስረድተዋል።  

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ለማኀበራዊ እና ለምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ እየሰጠ ያለው ጠቃሜታ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ተመራማሪው፤ መላው ሕብረሰተብም ችግኝ በመትከል እና በመንከባከብ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

 

በላሉ ኢታላ

 #EBC #ebcdotstream #Greenlegacy #Adama