የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክን በደማቅ ቀለም ዳግም ጽፏል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው ትዕይንት ተራ የመምረጥና የመመረጥ ሂደት ሳይሆን፣ የማይበገረው የኢትዮጵያውያን ጽናት፣ ጥልቅ ሀገር ወዳድነትና የዴሞክራሲ ጥማት የታተመበት የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መራጩን ሕዝብ፣ “ይህ ሕዝብ ድንቅ ነው፣ ይህ ሕዝብ ተዓምረኛ ነው፤ ከፈጣሪ በቀር የዚህን ሕዝብ የልብ ትርታና የጽናት ጥልቀት አሟልቶ ሊረዳ የሚችል ምድራዊ ኃይል የለም” ሲሉ ገልጸውታል።
ትናንት በድምፅ መስጫው ዕለት የታየው ትዕይንት፣ ለዓለም ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም፣ ዜጎቻችን የሌሊቱ ቅዝቃዜና ጨለማ ሳይበግራቸው፣ የቀትሩ ፀሐይና ድንገተኛው ዝናብ ሳይከለክላቸው፣ ረጃጅም ሰልፎችና የእግር ድካም ሳይገታቸው በነቂስ ወጥተው መርጠዋል።
እናቶች ሕፃናትን አዝለው፣ አዛውንቶች በምርኩዝ ተደግፈው፣ አካል ጉዳተኞችና ሕመምተኞች በፅኑ ተስፋ ተሞልተው ለፈለጉት ዕጩ በነፃነት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
የጠላት ጩኸትና ማስፈራሪያ ሳይበግረው፣ በብዙ ውጣ ውረዶች መካከል የታየው ይህ የመራጮች ጽናት ለኢትዮጵያ ሕልውና የተከፈለ ታላቅ የዴሞክራሲ መሥዋዕትነት ነው።
በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ አሸናፊው ማንም ይሁን ማን፣ ዋነኛው ድል አድራጊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በመሆኑም፣ በምርጫው አሸንፎ ሀገርን ለመምራት ዕድሉን የሚያገኝ ማንኛውም አካል የሚሸከመው አደራ እጅግ ከባድና ቅዱስ ነው።
ለዚህ ታላቅ ሕዝብ ክብር የሚመጥን አገልግሎት መስጠት የሞራል ግዴታ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ "አደራ" ግልጽ ነው፤ "ያከበራችሁን ሕዝብ አክብሩ፤ በታመነው ልክ ተገኝታችሁ በንጽሕናና በቅንነት አገልግሉ!" የሚል
ይህን ታላቅ ሕዝብ ማገልገል ትልቅ መታደል ነው።
ሕዝቡ በከፍተኛ ትዕግሥትና ብርታት የሰጠውን ድምፅ ወደ ተጨባጭ ልማት፣ ሰላምና ብልጽግና መለወጥ ከተመራጮች የሚጠበቅ ታሪካዊ ግዴታ ነው።
ለዚህም፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አርዓያ የሚያደርጉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና የዴሞክራሲ ግንባታ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ ብቸኛው አማራጭ ነው።
ኢትዮጵያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደ ባላንጣ ሳይሆን እንደ አንድ ቡድን ተጫዋች በማየት፣ ከታችኛው እርከን እስከ ፌደራል ተቋማት በአመራር በማሳተፍ እና በማቀፍ የጀመረችውን አዲስ የፖለቲካ ባህል ማጠናከር ለሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ነው።
ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር "ተግቶ መሥራትና ሳይሰንፉ መሮጥ" የግድ ይላል።
ከአካባቢ ጥበቃና ከአረንጓዴ ዐሻራ እስከ ግዙፍ የኢኮኖሚ ግንባታዎች፣ ከማኅበራዊ ፍትሕ እስከ ተቋማዊ ሪፎርሞች የተጀመሩ ስኬታማ ሥራዎች የሕዝባችንን የነገ ተስፋ የሚያለመልሙ ናቸው።
አዲሱ መንግሥት እነዚህን ጅምሮች በማስቀጠልና በማሳደግ የሕዝቡን የኑሮ ጫና የሚቀንሱ፣ ሰላምን የሚያረጋግጡና የኢትዮጵያን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ማተኮር ይኖርበታል።
በላሉ ኢታላ