አቶ ኤቢሳ ኦሊ በነቀምቴ ከተማ የሶርጋ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡
ሀገራዊው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የፈጠረውን ሰፊ ዕድል በመጠቀም ሕይወታቸውን በከፍተኛ ደረጃ መቀየር ችለዋል።
አቶ ኤቢሳ ለዘመቻው የሚውሉ ልዩ ልዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ችግኞችን በማፍላት እና ለገበያ በማቅረብ የ24 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ይህ የስኬታቸው ጉዞ የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ በሀገራችን መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሲሆን፣ የተለያዩ የውጭ ሀገር እና የሀገር ውስጥ የችግኝ ዝርያዎችን እያላመዱ ለገበያ ያቀርባሉ።

በዚሁ ግቢያቸው ከሚያፈሉት ችግኝ ጎን ለጎን በወተት ላም እርባታ ሥራም የሚሠሩ ሲሆን፣ የሚያለሟቸው ችግኞች በሚያፈሩት አበባ በመታገዝም ዘመናዊ የንብ ማነብ ሥራን ያከናውናሉ።
በዚህም የአረንጓዴ ዐሻራ እና የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሮችን በማጣመር የቤተሰባቸውን ኑሮ በላቀ ደረጃ አሻሽለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ እና የሌማት ትሩፋት ሚሊየነር ያደረጋቸው አቶ ኤቢሳ፣ ዘንድሮ ብቻ ከ100 ሺህ በላይ የችግኝ ዓይነቶችን አዘጋጅተዋል።

የጀመሩትን ይህን ውጤታማ የልማት ሥራ ይበልጥ ለማስፋፋት እና ተደራሽነቱን ለማሳደግም በከፍተኛ ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት እየሠሩ እንደሚገኙ ኦቢኤን ዘግቧል።