በጌዴኦ ባህል ሦስት ነገሮች የህይወት መርህ ተደርገው ይወሰዳሉ። እነርሱም ቡና፣ እንሰትና ዛፍ ናቸው። በዚህም ሦስቱን በማቀናጀት ማሕበረሰቡ በጠባብ መሬት ብዙ ምርት የሚያገኝበትን የጥምር ግብርናን መከወን ችሏል።
የሕዝቡ ዕሴት የሆነው ባህላዊ የመልክዓ ምድር አያያዝ ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ መዝገብ ውስጥ ተካትቶ የዓለም ቅርስ ሆኗል።
ውጤቱ ታዲያ እንዲሁ በችሮታ የተገኘ ሳይሆን የጌዴኦ 'ባቦ' ሥርዓት ለዚሁ መነሻ ነው። 'ባቦ' አቻ ትርጉሙ ደን ማለት ሲሆን፣ ሥርዓቱም ደንን ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ በውስጡ ይይዛል።
በ'ባቦ' ሥርዓት ዛፍ በዘፈቀደ አይቆረጥም፤ ግለሰብ በራሱ ይዞታ ያለማው ዛፍ ቢሆንም እንኳን በሚቆረጠው ምትክ ከአራት በላይ ችግኞችን አስቀድሞ መትከል ይኖርበታል። 'ባቦ' ጥቂት የዛፍ አይነቶች ላይ ብቻ የማያተኩር፣ ሥነ ምህዳር ለሚያሻሽሉ ዛፎች ልማትና ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጥም ሥርዓት ነው።

ይህ ባህል ከአካባቢው አልፎ ለሀገር ጭምር አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑን የገለጹት የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር)፣ በአካባቢው የ'ባቦ' ሥርዓት በመተግበሩና ጥምር ግብርና በመስፋፋቱ የይርጋጨፌ ቡና ጣዕም ተወዳጅ ሆኖ እንዲዘልቅ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት።

ዛፍን እንዳሻኝ እተክላለሁ ማለትም በዚህ ሥርዓት የተከለከለ ሲሆን፣ ከቡናና ከእንሰት ጋር የሚዛመዱ፣ ለዕድገታቸው በጎ ተፅዕኖ ያላቸው እንዲሁም የአፈር መሸርሸርን የሚከላከሉ እንዲሆኑ ይጠበቃል።
‘ባቦ’ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጣውን ተፅዕኖ መቋቋም የሚችል በመሆኑ ለሌሎች ትምህርት ሰጪ እንደሆነ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ እንደ ሀገር ብዙ የተሰራበትና ውጤት ያስገኘው አረንጓዴ ዐሻራ ኩራታችን እንደሆነ ሁሉ፤ የበለጠ ለመስራት በየአካባቢው ያለው የደን አጠባበቅ ሥርዓት መተዋወቅ አለበት ብለዋል።
ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወጣት ሚስት ማግባት ቢፈልግና ሽማግሌ ቢልክ ከሚቀርበው ጥያቄ አንዱ ልጄን የሚያገባው ሰው ዛፍ አለው ወይ? ዛፍ መትከል ይወዳል? የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል። በአካባቢው ዛፍ መትከልና መንከባከብ የጋብቻ መስፈርት ሆኖም ያገለግላል።

የጌዴኦ ሕዝብ የ'ባቦ' ሥርዓት በባህላዊ አስተዳደር ጥበቃ የተደረገለትና በሀገር በቀል ዕውቀት የተቃኘ በመሆኑ አረንጓዴ ምድር ፈጥሯል።
በኢትዮጵያ በሀገር በቀል ዕውቀት ከሚተገበሩት እንደ 'ባቦ' ካሉ ነባር የደን አጠባበቅ ሥርዓቶች ዓለም ብዙ ትምህርት መውሰድ ይችላል።
በሲሳይ ደበበ