Search

አረንጓዴ ተአምር - የትውልድ ጥሪ!

እሑድ ሰኔ 14, 2018 50

 

በአንድ ወቅት፣ "መንግሥት ችግኝ ከመትከል ሌላ ተግባር የለውም ወይ? ይህ የመንግሥት ሥራ አይደለም!" የሚሉ የነቀፌታ እና የትችት ድምፆች በአደባባይ በስፋት አስተጋብተው ነበር። ብዙዎች ይህንን አረንጓዴ ራዕይ ገና ሲጀመር አጣጥለውት፣ ጥቂት ተክሎ የሚያበቃ የፖለቲካ ዘመቻ መስሏቸው ፊታቸውን አዙረውም ነበር።

ዛሬ ግን መሠረተ ቢስ ትችት ወደ አድናቆት፣ ጥርጣሬ ደግሞ ወደ ታላቅ የትውልድ ንቅናቄ ተቀይሯል። የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ "አረንጓዴ ዐሻራ ማሳረፍ የትውልድ ተልዕኮ ነው" ብሎ በጽኑ በማመን፣ ንቅናቄውን ከዘመቻነት አልፎ ወደ ቋሚ ባህል እና የሕይወት ዘይቤነት አሸጋግሮታል። ይህ በገሀድ እያየነው ያለው "አረንጓዴ ተአምር" ነው።

ይህ ተአምር የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር በአዲስ ውበትና በአዲስ የሕይወት እስትንፋስ እያደሰ ይገኛል። በመላ ኢትዮጵያ፣ ሰማይ ጠቀስ ግርማ ሞገስ ካላቸው ተራራማ ስፍራዎች እስከ ዝቅተኛ ቆላማ እና በረሀማ ቦታዎች፣ እንዲሁም በየወንዙ ዳርቻዎች ሁሉ ይህ አረንጓዴ ማዕበል በስፋት እየተሰራጨ ነው።

ይህ ጉዞ ተራ የተፈጥሮ ጥበቃ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያን የምድር ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እና የተፈጥሮ ሀብቷን በማስመለስ የነገዋን ተስፋ በጠንካራ ዓለት ላይ ለማቆም የሚደረግ የሕልውና ትግል ነው።

በዚህ ታላቅ ሀገራዊ መድረክ ላይ፣ ተመልካች የሆነ ማንም የለም። መሪዎች ከሕዝባቸው ጋር አብረው ሲተጉ፣ ቤተሰቦች ከነልጆቻቸው የነገን ተስፋ ሲተክሉ ይታያሉ። አዛውንቶች በምርቃት፣ የሃይማኖት መሪዎች በጸሎት፣ ወጣቶች እና ጎልማሶች በማይነጥፍ ጉልበታቸው፣ ተማሪዎች በዕረፍት ጊዜያቸው በዚህ ታሪካዊ ጉዞ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ተሰልፈዋል።

ሕፃናት ችግኝ ሲያቅፉ፣ የተራቆቱት ተራሮቻችን ዳግም የሕይወት እስትንፋስ ሲያገኙ ማየት የዘመናችን ትልቁ ሥነ ልቦናዊ ድል ነው።

ተፈጥሮን ማዳን፣ ትውልድን ማሻገር ነው። አረንጓዴ ዐሻራ የትናንት ስብራታችንን የምንጠግንበት፣ የዛሬን አንድነታችንን የምናጸናበት እና የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ የምንገነባበት የጋራ መርከባችን ሆኗል።

ይህ ተአምራዊ ጉዞ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል። እኛ ኢትዮጵያውያን ተስፋን መትከል ባህላችን አድርገናል፤ ልምላሜን ማረጋገጥ ደግሞ የሕልውናችን መሠረት ሆኗል።

በተለይም በዚህ 2018 . የክረምት ወቅት፣ ምድሪቱ ዝናብን ተስፋ አድርጋ አፏን ከፍታ በምትጠብቅበት በዚህ ጊዜ፣ የተጀመረውን የድል ጉዞ ወደ አዲስ ከፍታ ለማሸጋገር መላው ሀገር ተነቃቅቷል።

የዚህ ታሪካዊ የአረንጓዴ ተአምር አካል ለመሆን ለክረምት ተዘጋጅተዋል? የትውልድ አደራዎን ለመወጣት፣ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ሕያው ዐሻራዎን ለማሳረፍ የችግኝ ጉድጓድዎን ቆፍረዋል? መልሱ ያለው እርስዎ ዘንድ ነው!

ጊዜው አሁን ነው፤ ይነሡ! ተስፋን ይትከሉ፤ ኢትዮጵያን የሚያክመውን አረንጓዴውን ተአምር ይቀላቀሉ!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ