Search

አባት - መዝገበ-ቃላት የማይፈቱት ረቂቅ ቃል

እሑድ ሰኔ 14, 2018 55

ዛሬ ልዩ ቀን ነው፤ ፍቅሩን በቃላት ሳይሆን በተግባር፣ በላቡ እና በድካሙ ለሚያሳየን ልዩ ሰው ለሆነው አባት የተሰጠ ቀን።

አባት ብዙም የማይነገርለት ጀግና ነው። ሲደክመው 'ደከመኝ' የማይል፣ የራሱን ሕልም ወደ ጎን ትቶ የልጆቹን ሕልም ለማሳካት ሌሊት ከቀን የሚለፋ የቤተሰብ ዋልታ ነው።

'አባባ' የሚለው ቃል ከጀርባው ስንት መሰጠት፣ ስንት አባጣ ጎርባጣ መንገድ ማለፍን እንዳዘለ የምንረዳው እኛም ስናድግ ነው።

ጠንካራ ተግሳጹ የነገ የሕይወት ስንቅ የሚሆንበት፣ ሻካራ መዳፉ ደግሞ ከምንም በላይ አስተማማኝ መጠጊያችን ነው።

አባት ማለት የቤተሰብ መሠረት፣ የትውልድ መነሻ እና መዝገበ ቃላት ሊፈቱት የማይችሉት ረቂቅ የሕይወት ምስጢር ነው።

ዛሬ በመላው ዓለም የምናከብረው የአባቶች ቀን ታሪካዊ መነሻው፣ በጦርነት እሳት ውስጥ ካለፈ ጽናት ጋር የተያያዘ እና እጅግ ልብ የሚነካ ነው።

ታሪኩ የሚጀምረው የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ዐርበኛ ከነበረው ዊሊያም ስማርት ከተባለ አንድ ብቸኛ አባት ቤት ውስጥ ነው።

ዊሊያም በጦርነቱ ሜዳ ላይ የነበረውን ከባድ ውጊያ እና መከራ በጽናት ተጋፍጦ ካለፈ በኋላ፣ ወደ ቤቱ ሲመለስ ግን ሌላ የሕይወት ጦርነት ገጠመው።

ባለቤቱን በሞት ተነጥቆ፣ አንድ አራስን ጨምሮ ስድስት ሕፃናት ልጆቹን ሌላ ትዳር ሳይመሠርት ብቻውን በፍቅር እና በእንክብካቤ ማሳደግ ነበረበት። ከጦርነቱ ሜዳ ይልቅ በቤቱ ውስጥ የገጠመውን ድምፅ አልባ የኑሮ ተጋድሎ በታላቅ አባትነት አሸነፈው።

ይህንን የአባቷን በጦርነት የተፈተነ ጽናትና ድምፅ አልባ መሥዋዕትነት እያየች ያደገችው ልጁ ሶኖራ፣ የአባቷ የላብ ጠብታዎች ያለ ዕውቅና ማለፍ የለባቸውም ብላ ባደረገችው ያላሰለሰ ትግል በዓሉ ሊመሠረት ችሏል።

አባት የሕይወታችን የመጀመሪያው መሪና መጋቢ ነው። በምንራመድበት የሕይወት ጎዳና ላይ አቅጣጫ እንዳይጠፋን በእርምጃው፣ በትዕግሥቱ እና በጽናቱ ቀናውን መንገድ መርቶናል።

የእነሱ ሻካራ እጆችና የትከሻ መጉበጥ፣ የእኛ ሕይወት የተደላደለ እንዲሆን የከፈሉት የዘላለም ዋጋ ማኅተም ነው።

እኛ ዛሬ በሕይወት አደባባይ ከፍ ብለን የታየነው፣ በትናንትናው የባቶቻችን መሥዋዕትነት ትከሻ ላይ ስለቆምን ነው።

ትልቁ እና ከባዱ ጸጸት የሚመጣው አባታችን ከአጠገባችን በሌለ ጊዜ ነው፤ ስለሆነም ዛሬውኑ ከአጠገባችን እያሉ ፍቅራችንን በጊዜ እንግለጽላቸው።

ለእነሱ የከበረ ቁሳዊ ስጦታ አያስፈልጋቸውም፤ የእነሱ ትልቁ ሽልማት የደከሙበት ልጅ ቀና ብሎ ሲሄድ እና የእነሱን ስም በክብርና በኩራት ሲያስጠራ መመልከት ብቻ ነው።

በሕይወት ላሉት አባቶቻችን ክብር፣ ፍቅር እና ምስጋና እንስጥ። በሞት የተለዩንን ደግሞ የተውልንን ዐሻራ እና መልካም ስም እያሰብን እናክብራቸው።

መልካም የአባቶች ቀን!

በሔዋን ጌታቸው