ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የጀመረችው ጉዞ አሁን ላይ ተጨባጭ ፍሬዎችን ማፍራት ጀምሯል።
ሀገራችን በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ስር የጀመረቻቸው መጠነ-ሰፊ ንቅናቄዎች በተለይም የወጣቱን የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት እየተተገበረ ያለው የ"አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ ለነገው የዲጂታል ኢኮኖሚ ጠንካራ መሰረት እየጣለ ይገኛል።
ይህ የክህሎት ልማት ሥራ በሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይቀር የዜጎችን ሕይወት ከሚያቀልሉ ዘመናዊ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ጋር ተቀናጅቶ መምጣቱ የትራንስፎርሜሽኑን ፍጥነት ያሳያል።

ለዚህ ትልቅ ማረጋገጫ የሚሆነው ደግሞ "ዲጂታል ለልህቀት" በሚል ስያሜ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረው በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው መሶብ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ ነው።
ይህ ስኬት ለሀገራችን ከፍተኛ ኩራት ከመሆኑም በላይ፣ በቴክኖሎጂ የሚመራ እና ዓላማ ተኮር ኢንቨስትመንት ምን ሊያስገኝ እንደሚችል በተግባር ያረጋገጠ ነው።
የመሶብ መተግበሪያ እና የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋነኛ ፋይዳ ዜጎች ከተለያዩ የመንግሥት እና የንግድ ተቋማት የሚፈልጓቸውን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች በአንድ መድረክ ላይ ማግኘት ማስቻሉ ነው።
ይህ አሠራር ለዘመናት የቆየውን እና የሕዝብን እንግልት የሚጠይቀውን የተንዛዛ ቢሮክራሲ ከማስቀረት ባለፈ የዜጎችን ጊዜ ይቆጥባል፣ የሙስና ቀዳዳዎችን ይደፍናል፣ እንዲሁም በመንግሥት በኩል የተቋማትን ታማኝነት እና ጥንካሬ ያጎለብታል።
ማዕከሉ የወረቀት አልባ አሠራርን እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን በተግባር በማሳየት ረገድ የአገልግሎት አሰጣጥ አብዮት ፈጣሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በተጨማሪም ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን፣ የኢ-ኮሜርስ አማራጮችን እና የቴክኖሎጂ ትስስሮችን በአንድ ላይ በማጣመር የንግድ እንቅስቃሴን ከማቀላጠፉም በላይ የፋይናንስ ዘርፉን ዘመናዊነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጉዞ ከፖሊሲ እና ከስትራቴጂ አልፎ የኢኮኖሚ ወሳኝ መሰረተ-ልማት የሆነውን መሶብን እውን አድርጓል፡፡
ይህም የሀገራችን ትልሞች ተራ ምኞት ሳይሆኑ በገዛ እጃችን እና አቅማችን የምንገነባቸው እውነታዎች መሆናቸውን በግልጽ አሳይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንዳሰመሩበት ይህን ታላቅ ስኬት ይበልጥ በማጠናከር የተገኘውን ተሞክሮ ለአፍሪካውያን ወንድሞች እና እህቶች ማካፈል፣ እንዲሁም ከዚህ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መሥራት የሁሉም ኃላፊነት ነው።
የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ፣ አሠራርን ማዘመን እና የዜጎችን አመኔታ መገንባት የዚህ ስትራቴጂካዊ ጉዞ ዋና ግቦች ሆነው ይቀጥላሉ።
በሔዋን ጌታቸው