የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሀገር በቀል ቴክኖሎጂ የታገዘ ስኬታማ ሥራ ማከናወኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ አስታውቀዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ እየተካሄደ ባለው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አጠቃላይ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ-ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቦርዱ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርጫው ዕለት እንዲሁም በድህረ ምርጫው ሂደት አስፈላጊውን ዝግጅት በከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በተለይም አካታችነትን ዋና መርሕ በማድረግ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ በተለይም የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውንና በምርጫው ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት እና መርሐ-ግብር ወጥቶ መተግበሩን አስገንዝበዋል።
ምርጫ ቦርዱ የተጠቀማቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በሀገር በቀል ባለሙያዎች የበለጸጉ መሆናቸውን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፣ ይህም በቀጣይ አስፈላጊውን ማሻሻያ ለማድረግ እና የመረጃዎችን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው አብራርተዋል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በምርጫው ወቅት ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥሰቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ትልቅ እገዛ ማድረጋቸውንም አክለዋል።
በሂደቱ የ10 ሺህ 438 ዕጩዎችን በጥራት አጥርቶ ማካተት እጅግ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም፣ በከፍተኛ ትኩረት ተሠርቶ ስኬታማ ውጤት እንዲመዘገብ መቻሉን ገልጸዋል።
የቦርዱን ነጻነት እና ተዓማኒነት በተመለከተም፣ ቦርዱ በሥራው ላይ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆኖ ውሳኔዎችን ሲወስን መቆየቱን ሰብሳቢዋ አረጋግጠዋል።
አያይዘውም ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን ከምርጫ ውጭ ባሉ ጊዜያትም ጭምር በተሻለ ሁኔታ ተቀራርቦ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በምርጫው ሂደት ወቅት የተሳሳቱ መረጃዎች (misinformation) በስፋት መሰራጨታቸው ቦርዱን በከፍተኛ ሁኔታ የፈተነው ዋነኛ ተግዳሮት እንደነበር ሰብሳቢዋ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፈው ምርጫውን ስኬታማ እንዲሆን ጥረት ላደረጉ የምርጫ ቦርድ አባላት እና ሠራተኞች ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
በለሚ ታደሰ