ከ130 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ሕዝብ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ እና የዘመናዊ ንግድ መስተጋብርን ለማሳለጥ፣ የባሕር በር መዳረሻ መኖሩ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።
የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን በማቀላጠፍ፣ የንግድ ወጪን በመቀነስ እና ዓለም አቀፍ የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የባሕር በር የማይተካ ሚና አለው።
በዘመናዊው ዓለም የንግድ እንቅስቃሴ፣ ከጠቅላላ የዓለም ንግድ ልውውጥ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው በባሕር ትራንስፖርት አማካይነት ይከናወናል።
ለትልቅ ሕዝብ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን፣ ነዳጅን እና የፍጆታ ቁሳቁሶችን በብዛት እና በዝቅተኛ ዋጋ ለማጓጓዝ የባሕር በር አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው።

ይህም የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ ለላኪዎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በአንፃሩ የባሕር በር ማጣት በንግድ መስመሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሎጂስቲክስ እና የትራንስፖርት ወጪን ይጭናል።
ይህ ተጨማሪ ወጪ በቀጥታ በሸቀጦች መሸጫ ዋጋ ላይ በማረፍ የዜጎችን የመግዛት አቅም ይፈታተናል።
በቀጥታ የባሕር መዳረሻ ማግኘት እነዚህን አላስፈላጊ ወጪዎች በመቀነስ የንግድ ቅልጥፍናን ከመጨመሩም በላይ፣ የዋጋ ግሽበትን በማረጋጋት የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የባሕር በር ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር የጂኦ-ፖለቲካዊ እና የደኅንነት ትስስር ማዕከል ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ፈተና በበዛበት ቀጣና ላይ ለሚገኝ ሀገር ባሕር በር ለንግድ ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ እና ቀጣናዊ ደኅንነት እጅግ ወሳኝ ነው።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ የባሕር መዳረሻን መጠቀም በጋራ ጥቅም እና በሰላም ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ያጠናክራል።
ይህ ዓይነቱ ትስስር ንግድን ከማሳለጥ ባለፈ የሁለገብ አጋርነትን በመፍጠር፣ በክልሉ ውስጥ የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት እንደ መሰረት ያገለግላል።
በመሆኑም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን እና የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ለማቀላጠፍ የባሕር በር መዳረሻ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ አጀንዳ ነው።
በሃና ምንዳሁን