Search

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በሰጡት መግለጫ ምን ምን ጉዳዮችን አነሱ?

ማክሰኞ ግንቦት 25, 2018 280

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ ከድምፅ መስጫ ቀን በኋላ ያለውን አጠቃላይ የምርጫ ሂደት ሁኔታና ቀጣይ ሥራዎችን አስመልክተው በሰጡት ማጠቃለያ መግለጫ በርካታ ዋና ዋና ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ሰብሳቢዋ በመግለጫቸው ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

የድምፅ አሰጣጥ እና የቆጠራ ሂደት ወቅታዊ ሁኔታ፦ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን የተከናወነው የድምፅ መስጠት ሂደት በአብዛኛው በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ የተወሰኑ ክልሎች በሰዓቱ አጠናቀው ወዲያውኑ ወደ ቆጠራ መግባታቸውንና አንዳንዶቹ ደግሞ ቆጠራውን አሳድረው ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ በነበረው ረጅም ሰልፍ ምክንያት ቦርዱ እስከ ሌሊቱ 600 ሰዓት ድረስ የጊዜ ማራዘሚያ ማድረጉንና በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እንዲሁም በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በአማራ እና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች አሁንም በድምፅ ቆጠራ ሥራ ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

የመዘግየት ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች፦ በአዲስ አበባ የተስተዋለውን የሰልፍ መርዘምና የመዘግየት ችግር ለመፍታት ቦርዱ በርካታ ከፍተኛ ባለሙያዎችንና ኤክስፐርቶችን ወደ ጣቢያዎች መድቦ እንደነበር ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል፡፡

ለመዘግየቱ እንደ ምክንያት ያነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች በመራጮች መዝገብ ላይ ስም የመፈለግ ሂደት መርዘም እና በአንዳንድ ጣቢያዎች የዕጩዎች ቁጥር እስከ 123 መድረሱ መራጮች በምስጢር ድምፅ መስጫ ክፍል ውስጥ የሚወስዱትን ደቂቃ ማርዘሙን ነው፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍም ቦርዱ ተጨማሪ የድምፅ መስጫ ሳጥኖችንና ቡዞችን ወደ ጣቢያዎች ልኮ መፍትሔ ለመስጠት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ቅሬታዎችን ማስተናገድና የተወሰዱ የቅጣት እርምጃዎች፦ ቦርዱ በሕግ ክፍል፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች የሥራ ክፍል፣ 6412 የጥሪ ማዕከልና ከታዛቢዎች በሚደርሱት ጥቆማዎች መሠረት የርምትና የማጣራት እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ሜላትወርቅ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች መግባት የሌለባቸው ሰዎች ስለመታየታቸው የቀረቡ ጥቆማዎችን ቦርዱ በሞኒተሪንግ ቡድን አጣርቶ እውነት ሆነው በተገኙት ላይ እርምጃ መውሰዱንና ሕግና ደንብ ጥሰው የተገኙ የምርጫ ጣቢያ ሠራተኞችን ማሰናበቱን አረጋግጠዋል፡፡

የውጤት አሰጣጥ እና የማረጋገጥ ቀጣይ ሥራዎች፦ በአሁኑ ወቅት የምርጫ ውጤታቸው በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ተደምሮ ያለቀላቸው ውጤቶች በየጣቢያዎቹ ተለጥፈው ለሕዝብ ይፋ መደረጋቸውን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፣ ቀጥሎም ውጤቶቹ ወደ ምርጫ ክልል ሄደው የማዳመር ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ውጤቶቹ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት የማረጋገጫ ማዕከል ከመጡ በኋላ፣ ከተመዘገበው የመራጭ ቁጥር አንጻር ዋጋ ያላቸው እና የሌላቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ተለይተው የማረጋገጥ ሥራው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ቦርዱ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡