የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) የኢትዮጵያን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ያዘጋጀውን የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ምልከታ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደረሰው ጥሪ መሠረት 26 አጭር ጊዜ ታዛቢዎችን ያቀፈ ቡድን በማሰማራት ሂደቱን ሲከታተል የቆየው ተቋሙ፣ በምርጫው የታዩ አስተዳደራዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ማሻሻያዎችን አወድሷል።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው በዚህ ምርጫ ወቅት የተወሰኑ የፖለቲካ እና የፀጥታ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት ምርጫው ሊካሄድ ከነበረባቸው 557 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ501ዱ ላይ ብቻ የተከናወነ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በ52,044 የክልል እና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ ተሰጥቷል።
የኢጋድ ታዛቢ ቡድን ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ምርጫ በማዘጋጀት እና በማስፈጸም ረገድ ያሳየውን ከፍተኛ አስተዳደራዊ እና ተግባራዊ አቅም አድንቋል።
ቦርዱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን በ501ዱ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ወደ 52,000 የሚጠጉ የምርጫ ጣቢያዎችን በተሳካ ሁኔታ ሥራ ላይ ማዋል መቻሉን ቡድኑ በሪፖርቱ አመልክቷል።
በተለይም በምርጫው ሂደት ላይ የተስተዋሉ ዘመናዊ አሠራሮች የኢጋድን አድናቆት አትርፈዋል።
ከእነዚህም መካከል፦
* በጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት (GIS) ላይ የተመሠረተ የምርጫ ጣቢያዎች ካርታ ዝግጅት፣
* የተደባለቀ (ሀይብሪድ) የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት አጠቃቀም፣
* በሀገር ውስጥ ለተፈናቀሉ ዜጎች (IDPs) እና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የተዘረጉ ልዩ የድምፅ አሰጣጥ ማዕቀፎች ይገኙበታል።
እነዚህ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች የምርጫ ሂደቱን ለማዘመን፣ ይበልጥ ተደራሽ፣ አካታች እና ቀልጣፋ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ታዛቢ ቡድኑ ገልጿል።
በተጨማሪም የመራጮች ግንዛቤን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት 169 ድርጅቶች የመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ ዕውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፣ 114 ያህሉ ደግሞ ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘታቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ኢጋድ ይህ የምርጫ ሂደት በቀጠናው ያለውን ግልጽነትና ዲሞክራሲያዊ ትብብር ለማጠናከር ትልቅ እመርታ መሆኑን አስታውቋል።