ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ የዳያስፖራ ማኀበረሰብ አባላት ጋር የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ስኬታማ እንደነበር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የዲያስፖራ አስተባባሪ አቶ ረታ ጌራ ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኮሚሽኑ ዳያስፖራዎችን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደቱ ሲያሳትፍ የደቡብ አፍሪካው መድረክ የመጀመሪያው መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመድረኩ ኮሚሽኑ በ3 አይነት መንገድ አጀንዳው መሰብሰቡንም የገለጹት አቶ ረታ፤ በአካል በመገኘት የሚቀርቡ፣ ለኮሚሽኑ በቀጥታ በሚረከበው የአጀንዳ ሀሳብ እና በበይነ መረብ በሚደረግ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት እንደነበሩም አስረድተዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማሳተፍ የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ሰላማዊና አሳታፊ እንደነበርም ገልጸዋል።
የደቡብ አፍሪካው መድረክ ሀገራዊ የምክክር ሒደቱ አካታች መሆኑን በተሻለ መንገድ ያሳየበት እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡
ቀን ሙሉ የሚደረጉ የአጀንዳ የማሰባሰብ የውይይት ሒደቶች እንደነበሩም ነው የገለጹት፡፡
ደቡብ አፍሪካ በምክክር የተለያዩ ችግሮቿን የፈታች ሀገር በመሆኗ ከአጀንዳ ማሰባሰቡ ባሻገር የተለያዩ የልምድ ልውውጥ መደረጉንም ነው የተናገሩት።
የተሳታፊው ቁጥር በሚፈለገው መልኩ ማግኘት አንዱ ውጤት እንደሆነም ነው ያብራሩት፡፡
ኮሚሽነሮቹ በደቡብ አፍሪካ የነበራቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት አጠናቀው በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ መግባታቸውን አቶ ረታ ገልጸዋል።
በቅርቡም በአሜሪካ እና ካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት እንደሚጀመርም አስታውቀዋል።
በእንግሊዝ ፣ ስዊዘርላንድ ፣ የአረብ ሀገራት ላይም የምክክር አጀምዳ ማሰባሰብ ሒደቱ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአንጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ላይ በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሜሮን ንብረት
#EBC #ebcdotstream #NationalDialogue