Search

“የሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ መምረጥ የዴሞክራሲ ንቃቱን ያሳያል” - ኡስታዝ ጀማል በሽር

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 69

ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ጉጉት እና ተሳትፎ ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ መምጣቱን የኪንግስ ኦፍ ዓባይ (Kings of Abay) መሥራች እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪው ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ።

በተለይም ሚሊዮኖች በነቂስ ወጥተው ለምርጫ መመዝገባቸው እና መምረጣቸው፣ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ጉዞዋ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ መግባቷን የሚያመለክት ክስተት መሆኑን አስታውቀዋል።

ኡስታዝ ጀማል በኤፍ.ኤም አዲስ 97.1 ሬዲዮ ሀገር እንሥራ በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀ መድረክ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ቀደም ሲል ምርጫ ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የቀረበ ጉዳይ መስሎ ይታይ እንደነበር ጠቅሰው፣ ዛሬ ግን ሰፊው ሕዝብ በንቃት ወጥቶ መምረጡ የፖለቲካ ተሳትፎ እየሰፋ ሰለመምጣቱ ግልጽ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

“‘ማንን ምረጡ? ከሚል ይልቅ 'ተመዝገቡ፣ ድምፃችሁን አሰሙ' የሚለው መልዕክት በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ የንቃተ-ኅሊና ለውጥ ፈጥሯል ያሉት ኡስታዝ ጀማል፣ ይህ ጥሪ በእርሳቸውም ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ በሕይወታቸው ለሁለተኛ ጊዜ ለመምረጥ መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለምርጫ መመዝገባቸው እጅግ አስደናቂ ስኬት መሆኑን ገልጸው፣ ይህ የሕዝብ ተነሳሽነት በብዙ የተረጋጉ የዴሞክራሲ ሀገራት እንኳን በምዝገባ ወቅት በቀላሉ የማይታይ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ይህ ክስተት ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህልን እየገነባች መሆኗን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎች የሀገር ጉዳይ የሁሉም እንጂ የጥቂቶች ብቻ አይደለም' የሚል ግንዛቤ እያዳበሩ መምጣታቸውንም ያሳያል።

ሀገር ማለት የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ወይም ባለሥልጣን ብቻ አይደለም፤ አንድ ዜጋ በሰላም ወጥቶ መግባቱ፣ በነፃነት ሐሳቡን መግለጹ እና በሀገሩ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ መሆኑ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ኡስታዝ ጀማል በሽር በመጨረሻ እንዳሉት፣ ሀገርን ማስቀጠል የሚቻለው በጽንፈኝነት፣ በግጭት ወይም በጥላቻ ሳይሆን በሰላማዊ እና ሕጋዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ነው።

በዚህ ምርጫም ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅሞቻቸው ዙሪያ በጋራ መቆም እንደሚችሉ ያሳዩበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።

በሔዋን ጌታቸው