ታላላቅ የዓለማችን ከተሞች ሲነሱ ብዙውን ጊዜ ወንዞች አብረዋቸው ይነሳሉ፡፡ ምክንያቱም ወንዞች የውኃ ምንጭ ብቻ አይደሉም።
ወንዞች የከተሞች መለያ፣ የታሪክ ምስክር፣ የጥበብ ምንጭ፣ የኢኮኖሚ መሠረት እና የቱሪስት መስህብ ናቸው።
ብዙ የዓለም ታላላቅ ከተሞች በወንዞች ዳርቻ ተመስርተው ውበታቸውን ከእነዚህ ወንዞች አግኝተዋል።
ባለቅኔዎቻቸው እና ደራሲዎቻቸውም በወንዞቹ ተጠብበዋል። ለዚህ ደግሞ በሩሲያ ታሪክ እና ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው፣ የበርካታ ታላላቅ ደራሲያን እና ባለቅኔዎች የፈጠራ መነሳሻ እና የሥነ-ጽሁፍ ምንጭ የሆነው ማራኪው ቮልጋ ወንዝ አስደናቂ ማሳያ ነው።

በእንግሊዝ የሚገኘው ቴምስ ወንዝ ለለንደን ከተማ የልብ ምቷ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የከተማዋ ታሪክ፣ ንግድ፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ባህል እና ቱሪዝም ከዚህ ወንዝ ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡
በቴምስ ዳርቻ የተገነቡ የእግረኛ መንገዶች፣ መናፈሻዎች እና ታሪካዊ ሕንፃዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ይስባሉ።
የፈረንሳዩ ሴን ወንዝ ደግሞ የፓሪስ መለያ ነው። የአይፍል ታወር፣ የሉቭር ሙዚየም እና ሌሎች ታሪካዊ ቦታዎች ከዚህ ወንዝ ጋር ተያይዘው የከተማዋን ውበት ያጎላሉ።
የጀርመኑ ራይን ወንዝ በርካታ ከተሞችን ያስተሳስራል፡፡ በዳርቻው የሚገኙ ጥንታዊ አብያተ-መንግሥታት እና የወይን እርሻዎችም የአውሮፓ ቱሪዝም ትልቅ ሀብቶች ናቸው።
በሃንጋሪ የሚገኘው ዳኑብ ወንዝ ቡዳፔስትን ለሁለት ከፍሎ ከተማዋን የምሽት ፈርጥ እና ከዓለም ውብ ከተሞች መካከል አንዷ አድርጓታል።
በስዊዘርላንድ፣ ቱርክ እና ጣሊያን ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ወንዞች እና ዳርቻዎቻቸው ከውበት ባሻገር የከተማዎቹን የሥልጣኔ ጥግ ያሳያሉ።
በአሜሪካም የወንዞች ልማትም ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ነው። የኒውዮርክን ከተማ ውበት በእጅጉ ያጎላው ሃድሰን ወንዝ እና ከተማን የማደስ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው የቺካጎ ወንዝ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።
የእስያ አገራትም በወንዞቻቸው ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት በመሥራትና ውብ በማድረግ ይታወቃሉ።
በቻይና ሁዋንግፑ ወንዝ፣ በጃፓን የቶኪዮን ውበት ያደመቀው ሱሚዳ ወንዝ እንዲሁም በደቡብ ኮርያ የሚገኘው የሃን ወንዝ እና በሲንጋፖር የሚገኙ ወንዞች በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን ቱሪስቶች ይጎበኛሉ።
ሕይወት የዘሩት የአዲስ አበባ ወንዞች

በኢትዮጵያ በርካታ ታላላቅ ወንዞች ቢኖሩም፣ ወንዞችን አልምቶ ለከተማ ውበት እና አገልግሎት መጠቀም የዘመናት ክፍተት ነበር።
ለዚህ ደግሞ ለረጅም ጊዜ የቆሻሻ መጣያ ሆነው የነበሩትን የአዲስ አበባ ከተማ ወንዞችን መመልከት በቂ ነው።
አዲስ አበባ በርካታ ወንዞች አቋርጠው የሚያልፉባት ከተማ ናት። ቀበና፣ ቡልቡላ፣ አቃቂ፣ ቀርጡሚ እና ሌሎች በርካታ ወንዞች ከተማዋን አቋርጠው ይፈስሳሉ።
ከተማዋ ስትመሰረት እነዚህ ወንዞች ንጹሕ ስለነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች ይጠቀሙባቸው ነበር።
ሆኖም በጊዜ ሂደት የጨመረው የከተማው መስፋፋት በወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች መደበኛ ያልሆነ ሰፈራን አስከተለ፡፡
ይህ ሂደትም ንጹሕ የነበሩትን የአዲስ አበባ ወንዞች የከተማው ሀብት እንዳይሆኑ አድርጓቸው ቆይቷል።
የቤት እና የፋብሪካ ፍሳሽ፣ ፕላስቲክ እና የተለያዩ ተረፈ-ምርቶች ወንዞቹን ወደ ቆሻሻ መጣያነት ቀይረዋቸው ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአዲስ አበባ ወንዞች ወደ ቀደመ ታሪካቸው እና ክብራቸው የሚመልሳቸውን ጉዞ ጀምረዋል።
አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ የደመቁ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማት እና የዐረንጓዴ አሻራ ሥራዎች በአዲስ አበባ ወንዞች ላይ አዲስ ሕይወት እየዘሩባቸው ይገኛሉ።
ዛሬ የአዲስ አበባ ወንዞችን እንደ እነ ቴምስ፣ ሴን፣ ሃን እና ሁዋንግፑ ሁሉ የከተማዋ ውበት እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በርካታ አበረታች ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን ውጤቶቹም በተግባር መታየት ጀምረዋል።
የአዲስ አበባ ወንዞች ታሪክ ከብክለት ወደ እድሳት፣ ከመረሳት ወደ ትኩረት፣ ከቆሻሻ መጣያነት ወደ ከተማዋ ኩራትነት እየተቀየረ ነው።
ይህም ለከተማዋ ነዋሪዎች ሁሉ አዲስ መነሳሳትን እና ተስፋን የሚሰጥ ነው። የከተማዋ አስትንፋስ እየሆኑ የመጡት የአዲስ አበባ ወንዞች እንደ ዓለም ታላላቅ ከተሞች ወንዞች ሁሉ የቱሪዝም፣ የመዝናኛ እና የከተማዋ ውበት እውነተኛ ምልክቶች እንዲሆኑ ሁሉም በጋራ ሊንጠብቃቸው እና ሊያለማቸው ይገባል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ