በሚቀጥሉት ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገራችን አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ እንዳስታወቀው እርጥበታማው የአየር ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከረ በመምጣት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በመካከለኛው እና በደቡብ ምሥራቅ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል።
በተለይም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገራችን ክፍሎች ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አኃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።
በሌላ በኩል የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት በአፋር ክልል፣ በሰሜን እና በደቡብ ምዕራብ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ከ32 እስከ 40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ሆኖ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በመደበኛ ሁኔታ ወቅታዊው የክረምት ዝናብ ቀደም ብሎ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ አጋማሽ የሀገራችን ክፍሎች ላይ የሚጀምር ሲሆን፣ በሂደት እየተጠናከረ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ ሌሎች አካባቢዎችም እንደሚስፋፋ ተጠቁሟል።
በዚህም መሠረት በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በመካከለኛው እና በምሥራቅ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ ዝናቡ በመጠንም ሆነ በስርጭት የተሻለ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ይህ የሚኖረው እርጥበት ለግብርና ሥራ የማሳ ዝግጅት ለማድረግ፣ የመኸር ሰብሎችን ለመዝራት እንዲሁም ለበልግ ሰብል ተጠቃሚ አካባቢዎች መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገራችን ተፋሰሶች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው የገጸ ምድር የውኃ ፍሰት እንደሚኖርም ታውቋል።
በዚህም መሠረት በመካከለኛው እና ታችኛው አባይ፣ በላዩኛው እና መካከለኛው ባሮ አኮቦ፣ በላዩኛው ስምጥ ሸለቆ፣ በኦሞ ጊቤ፣ በአዋሽ እንዲሁም በገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ከመካከለኛ እስከ ከባድ የገጸ ምድር የውኃ ፍሰት እንደሚጠበቅ ተጠቅሷል።
በተመሳሳይ በላይኛው አባይ፣ በኦጋዴን፣ በመካከለኛው አዋሽ፣ በስምጥ ሸለቆ እና በኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የገጸ ምድር የውኃ ፍሰት እንደሚኖራቸውም ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ ገልጿል።