Search

በሰሜን ሸዋ ዞን እና ደብረ ብርሃን ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጥምር ፀጥታ ኃይሉ እና የሕዝቡ ቅንጅት ትልቅ ሚና ተጫውቷል

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 41

በሰሜን ሸዋ ዞን እና በደብረ ብርሃን ከተማ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጥምር የፀጥታ ኃይሉ፣ በፖለቲካ አመራሩ እና በሕዝቡ የተወሰደው ቁርጠኝነት የጎላ ሚና መጫወቱ ተገልጿል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (/) እንዳብራሩት፣ በዞኑ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከነበረው የመራጭ ቁጥር የሚልቅ ተመዝጋቢ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተመዘገበ ሲሆን፣ በድምፅ መስጫው ዕለትም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ድምፁን ሰጥቷል።

በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ፣ የመገናኛ ብዙኃን ለሕዝቡ ወቅታዊ መረጃን ተደራሽ በማድረግ የነበራቸው አስተዋፅኦ የሚደነቅ እንደነበርም በመድረኩ ተመላክቷል።

የደብረ ብርሃን ከተማ እና የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላም እና የምርጫ ተግባራት አፈጻጸም ተገምግሞ፣ የቀጣይ የሥራ ስምሪት የተሰጠበት የጋራ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩም አህመዲን መሐመድ (/) ጨምሮ በመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ፣ የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ እንዲሁም ሌሎች የዞንና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የመከላከያ እና የፀጥታ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከጥምር የፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን በሰሜን ሸዋ እና በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የጠላትን ዕቅድ በማክሸፍ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ማስቻሉን አስገንዝበዋል።

የፖለቲካ እና የፀጥታ መዋቅሩ በቅንጅት በመሥራቱ ሂደት ምርጫውን ያለምንም የፀጥታ ችግር ማስኬድ መቻሉን ያነሱት ሌተናል ጄኔራል ሹማ አሁንም አመራሩ ሳይዘናጋ የነበረውን ሰላምና ፀጥታ አጠናክሮ እንዲያስጠብቅ አሳስበዋል።

በብሩክ ተስፋዬ