Search

ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 44

ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሊቀ መንበር ብፁዕ አቡነ አንቶኒ የተመራውን ልዑካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የቮሎኮላምስክ ሜትሮፖሊታን እና የሞስኮ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሊቀ መንበር ብፁዕ አቡነ አንቶኒ ውይይቱን አስመልክተው ለኢዜአ እንደገለጹት ከፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ጋር የተሳካ እና ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሰች ታሪካዊ ሀገር መሆኗን ያነሱት ሊቀ መንበሩ አሁን ላይ በሀገሪቱ በመገኘታቸው ጥልቅ ደስታ እና ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው የረጅም ዘመን ታሪካዊ ግንኙነት በሁለቱ ተቋማትም ሆነ በሀገራቱ መካከል ለሚኖረው ዘላቂ እና ተስፋ ሰጪ ወዳጅነት ትልቅ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቁመዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም፣ ኢትዮጵያ ያካሄደችው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃና የተረጋጋ በሆነ መንገድ በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በበኩላቸው ውይይቱ የሁለቱን ሀገራት ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመና እጅግ ስኬታማ የነበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ትስስር በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ ከማሳደጉም ባለፈ፣ በሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ እና በልማት ጉዳዮች ላይ በቅንጅት ለመሥራት የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኤቭጌኒ ተሬኪን፣ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት መምሪያ የክርስቲያናዊ ግንኙነት ጉዳዮች ጸሐፊ ሂሮሞንክ ስቴፋን እንዲሁም የብፁዕ አቡነ አንቶኒ የግል ረዳት ቄስ አሌክሳንደር ኤርሾቭ ተገኝተዋል።