Search

ዓለም አቀፍ ተቋማት የመሰከሩለት የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 53

በሰላማዊነቱ እና በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎው ደማቅ ታሪክ ያስመዘገበው የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፥ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች እንዲሁም ከአውሮፓ ኅብረት እና ከአጋር ሀገራት ጠንካራ ዕውቅና እና አድናቆት አግኝቷል።

የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን መሪ የሆኑት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ሕዝቡ ከማለዳው ጀምሮ በከፍተኛ ፅናት እና እርጋታ ድምፁን መስጠቱን አድንቀዋል።

የአፍሪካ የነፃነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ ባሳየችው ዴሞክራሲያዊ አፈጻጸም ሕዝቧ እና መንግሥቷ በራሳቸው ሊኮሩ እንደሚገባ በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ፣ የኢጋድ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ (/) በሰጡት ምስክርነት፣ በሂደቱ የታየው አካታችነት፣ የመራጩ ሕዝብ የላቀ ትዕግሥት እና ሰላማዊ ድባብ ከዚህ ቀደም በየትኛውም ሀገር እንዳላጋጠማቸው ገልጸዋል።

ከምርጫው ጋር ተያይዘው የሚነሡ ማናቸውም ቅሬታዎች በሕጋዊ መንገድ ብቻ መፍታት እንዳለባቸው አሳስበው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም "ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" በሚለው መርሕ መሠረት ኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳያቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ ዕድል እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ከካናዳ፣ ኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ ጋር በጋራ ባወጣው መግለጫ የምርጫውን ስኬታማ ሂደት በደስታ ተቀብሏል።

ተቋማቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለእጩዎች ለሲቪል ማኅበራት እና ለፀጥታ ተቋማት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሙሉ ዕውቅና ሰጥተዋል።

እነዚህ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ምስክርነቶች፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን በጉልህ ያሳዩ ናቸው።

 በዮናስ በድሉ