ሁለተኛው የኢትዮጵያ እና ፊንላንድ የፖለቲካ ምክክር በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን በምክክሩ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ሰፊ ግምገማ ተደርጓል።
ምክክሩን በጋራ የመሩት አምባሳደር መለስ ዓለም እና የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ኦውቲ ሆሎፓይነን የሁለቱን ሀገራት የቆየ ግንኙነት እና አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
በዚሁ ወቅት ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር መለስ ዓለም በኢትዮጵያ ስላለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ስለ 7ኛው አጠቃላይ ምርጫ፣ ስለ ብሔራዊ ምክክር ሂደት እና ስለ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ለፊንላንድ ልዑካን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ የፊንላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ እና በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ በማቅረብ ንግድን ለማሳደግ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ምክር ቤቶች በቅርበት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ኦውቲ ሆሎፓይነን በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ እየታየ ያለውን ፈጣን የልማት ለውጥ አድንቀዋል።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ለሀገራቸው ቁልፍ አጋር መሆኗን ገልጸው፣ ፊንላንድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
በተለይም በዲጂታላይዜሽን፣ በከፍተኛ ትምህርት፣ በሜትሮሎጂ እና በአስተማሪዎች ሥልጠና ዙሪያ የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀው፣ መሰል መደበኛ ውይይቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።