Search

"ለራሳቸው የቆሙ እና ለሕዝብ የቆሙ ፓርቲዎችን የምንለይበት ጊዜ ነው"፦ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 101

የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲን ጥቅም በመረዳት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ማጠናቀቁን የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ተናገሩ።

ፕሮፌሰር ብሩክ ከኢቢሲ 'ዳጉ' ፕሮግራም ጋር ‹‹በምርጫ የምትገነባ እና የምትጸና አገር›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

በዚሁ ጊዜም የዴሞክራሲ ሥርዓት በጽኑ መሠረት ላይ ሊገነባ እና ቀጣይነት ያለው ባሕል ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። 

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ አፈጻጸም የታየበት እንደሆነ ያነሱት ምሁሩ፣ የመምረጥ መብት ኖሯቸው በተለያዩ ምክንያቶች ድምፅ ያልሰጡ ዜጎች መኖራቸው የሚያስቆጭ መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህ ምርጫ ለራሳቸው የቆሙ እና ለሕዝብ የቆሙ ፓርቲዎች የሚለዩበት አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የተወሰኑ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም አጠቃላይ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን ያብራሩት ፕሮፌሰር ብሩክ፣ ሁሉም አካላት በምርጫ መድረኩ ላይ ሀሳባቸውን በነጻነት ማንሳት እና ማንጸባረቅ የሚችሉበት ዕድል እንደነበር አስረድተዋል።

የሚመረጠው አካል በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ርክክብ ማድረግ እንዳለበት የገለጹት ምሁሩ፣ ተፎካካሪዎችም ሆኑ ገዢው ፓርቲ የሕዝብን ድምፅ ማክበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥራት ያለው ሥራ እየሠራ በመሆኑ ምስጋና እንደሚገባውም ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በውይይቱ ላይ በሰፊው አብራርተዋል። 

በሐና ምንዳሁን