የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፀጥታና ደኅንነት አፈፃፀም ሪፖርት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ተገምግሟል፡፡
በገምገማ መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እንደገለጹት፤ የጋራ ግብረ ኃይሉ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫው ወቅትና ከምርጫ በኋላ ያሉ ሥራዎችን እንደ ሀገር ዕቅድ አውጥቶ በቅንጅት በመመራቱ እንዲሁም የተናበበና ሰላምን ለማፅናት ጀግንነት የታየበት ተግባር በመፈፀሙ ምርጫው በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ በተሰራው ሪፎርም አሁን ላይ በተጨባጭ ትላልቅ ተልዕኮዎችን መሸከም የሚችሉ የፀጥታ ተቋማት መፈጠራቸውን በምርጫው ላይ የተመዘገበው ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የጋራ ግብረ-ኃይሉ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ጠላቶች የተቀናጀውን ከፍተኛ ሴራ ያከሸፈና የሀገርን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ በመሆኑ የሪፎርሙ ውጤት በተግባር የተለካበት መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራሉ አብራርተዋል፡፡

እንደ ፀጥታ ተቋም መኩራትና መመካት ያለብን በኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሪቱ ላይ እየሆነ ያለውን ተረድቶ፣ ሁሉንም በሚዛን አስቀምጦ፣ በምርጫው ቀን የሀገር አንድነት እና ሉአላዊነትን ያጸና ታላቅ ሕዝብ መሆኑን ያረጋገጠበት ምርጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሕዝቡ ከዚህ በኋላ መንግሥት በካርድ እንጂ በጥይት አይሆንም የሚል መልዕክት ማስተላለፉንም አክለዋል፡፡
በቀጣይም በሽብርተኞችና በፅንፈኞች ላይ የተጀመረው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል፡፡
የምርጫው ውጤት ታውቆ አዲስ የመንግሥት ምስረታ እስከሚከናወን እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ያሉ ሕዝባዊና መንግስታዊ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የፀጥታ ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የጋራ ግብረ-ኃይሉ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡