የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሊቀ መንበር ብፁዕ አቡነ አንቶኒ ሴቭሪዩክ የተመራውን የልዑካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱ ወቅት አቶ መሀመድ እድሪስ በሁለቱ ሀገራት፣ ሕዝቦች እና አብያተ ክርስቲያናት መካከል ዘመናትን ያስቆጠረና ልዩ የሆነ ሰላማዊ አብሮነትን ያጎላ ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን ገልጸዋል።

ይህ ለዓለም ምሳሌ የሆነ የጠበቀ ታሪካዊ ትስስር በቀጣይም በጋራና በትብብር ለመሥራት የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑን ሚኒስትሩ በአፅንኦት ማስገንዘባቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
የቮሎኮላምስክ ሜትሮፖሊታን እና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሞስኮ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሊቀ መንበር የሆኑት ብፁዕ አቡነ አንቶኒ ሴቭሪዩክ በበኩላቸው፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ወደተጠቀሰችው ታሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመምጣታቸው ጥልቅ የሆነ ደስታ እና ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ትስስር ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን የጠቀሱት ሊቀ መንበሩ፥ ይህም በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በሀገራቱ መካከል ለሚኖረው ታላቅ የወደፊት ተስፋ እና ትብብር አስተማማኝ ዋስትና መሆኑን ተናግረዋል።