Search

የዛሬው የዲጂታል ኢቢሲ ይፋ መሆን ሰፍቶ የመድረስ ፍላጎታችን መገለጫ ነው፦ አቶ ጌትነት ታደሰ

ረቡዕ ነሐሴ 07, 2017 169

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በዲጂታሉ ዘመን ራሱን የማብቃት ሥራ እየሠራ እና በዚህም አበረታች ውጤት እያሳየ ነው ሲሉ የተቋሙ  ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ገለጹ። 

ኢቢሲ በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ (አፕ) በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል። 

አቶ ጌትነት በመተግበሪያው ማስመረቂያ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢቢሲ ወደ ሁሉም ኢትዮጵያ እና አፍሪካ እንዲደርስ በሰፊው እየሠራ ነው፣ የዛሬው የዲጂታል ኢቢሲ ይፋ መሆንም ሰፍቶ የመድረስ ፍላጎታችን መገለጫ ነው ብለዋል። 

ኢቢሲ ወደ ይዘት በሚል መርሕ ባለፈው አንድ ዓመት ባደረገው የለውጥ ጉዞ በሁሉም የይዘት አማራጮች ስለኢትዮጵያ ልዕልና ለሁሉም ተደራሽ እየሆነ ነው ብለዋል። 

የይዘቶች ዋና ማጠንጠኛ ደግሞ ኢትዮጵያዊያንን የሚያቀራርቡ፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችሉ እና የሪፎርም ሥራዎችን የማግባባት ሥራዎች እንደሆኑ ነው ያብራሩት።

መልካም አስተዳደርን በተመለከተ የሕዝቡን ቅሬታ የሚዳስሱ አንደ ዐይናችን ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የሕዝብ ቅሬታን የሚፈቱ በርካታ መረጃዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያን ሆኖ የመጓዝ ጉዞአችንን ወደ ክልል በማስፋት እያሳካን ነው ያሉት አቶ ጌትነተ በደረስንበት ሁሉ ሕዝቡ በርቱ እያለ እያበረታታን ነው ሲሉ ገልጸዋል። 

"25 60 90 ብለን ኤፍ ኤም 97.1፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና የኢትዮጵያ ሬዲዮ የተጀመሩበትን ዓመታት እያከበርን ነው፤ በዚሁ መሐል ደግሞ የዲጂታል ዘመኑን የሚመጥን ሥራ እየሠራን ነው" ሲሉ ገልጸዋል። 

በኢቢሲ ወደ ይዘት ጉዟችን አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል ያሉት አቶ ጌትነት የእርሳስ ሲስተምን ጨምሮ 25 የዲጂታል መተግበሪያዎችን ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። 

"በብዙ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ወጪን በውስጥ አቅም ሠርተናል፤ ይህንን ማድረግ እንድችል ያደረጉት ደግሞ የኢቢሲ ጀግኖች ሲሉ የገለጿቸው ሠራተኞች ናቸው" ብለዋል። ለዚህም ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

በእርሳስ ከአጀንዳ መቅረፅ እስከ ዜና ውጤት ሥራ እንደሚመራበት ነው የገለጹት። ከዜና ጥቆማ እስከ ፕሮዳክሽን የሥራ ሂደትን የምንመራበት በመሆኑ የሚያኮራ ነው ብለዋል። 

ኢቢሲ ዶትስትሪም ከ50 በላይ መውጫዎች እንዳሉት ገልጸው ይህንን የተደራጀ ተቋም ለመመሥረት ብዙ አቅም መጠየቁን እና ለዚህም የተባባሪ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። 

በዲጂታል ኢትዮጵያ ማዕቀፍ ኢቢሲ ዶትስትሪም እንዲፈጠር ድጋፍ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።