7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ ሽግግር እና በሀገር ግንባታ ጉዞ ውስጥ የደረሰችበትን ወሳኝ ምዕራፍ ያሳየ ታሪካዊ ክስተት ነው።
ይህ የምርጫ ሂደት ሀገራችን የጀመረችው የተቋማት ግንባታ ስትራቴጂ ውጤታማነት፣ የዘመናዊ አስተዳደር አካላትን አቅም እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነት መዋቅሩን ፅናት በግልጽ አሳይቷል።
ሀገራችንን ያለ መንግሥት በማስቀረት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ ለመፍጠር የሞከሩ የውስጥ ታጣቂ ቡድኖች እና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ቀውስ ለፍጠር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የብሔራዊ ደኅንነት መዋቅሩ ግን በተቀናጀ ጥረት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በብቃት መከላከል ችለዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የተቋማዊ ብስለት ድል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ተጨባጭ ውጤት ነው።
የምርጫ ቦርድ ተቋማዊ አቅም፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና አስተዳደራዊ ጥንካሬ
በ2011 ዓ.ም በአዲስ መልክ የተዋቀረው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ከፍተኛ አቅም ያለው አስመራጭ ተቋም ሆኖ ተገንብቷል።
የቦርዱ ጠንካራ ሆኖ መውጣት የፌዴራል መንግሥቱ የተቋማት ግንባታ እና ትክክለኛ ፌዴራሊዝም ግንባታ አጀንዳ ዋና ማዕዘን ነው።
ተቋሙ 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ እንዲሁም አራት ሀገራዊ የክልል አደረጃጀት ሕዝበ ውሳኔዎችን በስኬት በማከናወን የሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን በሰላማዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ መንገድ መልሷል።
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አስተዳደራዊ ጥንካሬ እና የቴክኖሎጂ ዘመናዊነት በከፍተኛ ደረጃ የታየበት ነው።
ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ግልጽ የዕጣ ሥርዓት በመዘርጋት 24 የሬዲዮ እና 20 የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ጨምሮ በ66 የሚዲያ አውታሮች ላይ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት በማከፋፈል ፍትሐዊነትን አረጋግጧል።
በሂደቱም የተተገበሩት አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሠራሮች በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ የታዛቢዎች ልዑካን ዘንድ አድናቆትን አግኝተዋል።
ሌላው የቦርዱ አቅም የታየበት ጉዳይ ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት በመሥራት እያንዳንዱን ቅሬታ የፈታበት መንገድ ነው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በሩን ክፍት ማድረጉን እና ችግሮች ሲያጋጥሙ በመግባባት እየተፈቱ መምጣታቸውን ፓርቲዎቹ ራሳቸው ምስክርነት ሰጥተዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተቋማዊ ጥንካሬ እና ማዕከላዊ የፀጥታ ቁጥጥር
በዚህ ታሪካዊ የምርጫ ሂደት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ያሳየው ተቋማዊ ጥንካሬ ሌላው የሀገር ግንባታው ስኬት ማሳያ ነው።
ኮሚሽኑ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሀገራችን በሚገኙ 52 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች የፀጥታ አስከባሪዎችን እና ታክቲካል አባላትን በማሰማራት የምርጫውን ሠላማዊነት እና የዜጎችን ደኅንነት አረጋግጧል።
በተለይም ተቋሙ በቅርቡ የታጠቃቸውን የላቁ ዘመናዊ መሣሪያዎች በመጠቀም፣ እንዲሁም በመላ ኢትዮጵያ የሚደረጉ እያንዳንዱን እንቅስቃሴዎች በአንድ ማዕከል በመቆጣጠር ለምርጫው መሳካት ያደረገው አስተዋፅኦ የተቋሙን የደረጀ አቅም በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ይህ ማዕከላዊ የዕዝ እና የቁጥጥር ሥርዓት የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብን ደኅንነት በላቀ ሁኔታ እንዲጠብቅ፣ ክስተቶችን በቅርበት እንዲከታተል እና ለስጋቶች በፍጥነት ምላሽ በመስጠት እንዲያከሽፍ ትልቅ አቅም ፈጥሮለታል።
የተቀናጀው የደኅንነት እና የሳይበር ኦፕሬሽን ገድል
ይህ ግዙፍ ሀገራዊ ክንውን ሊሳካ የቻለው በፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማት ጥንካሬ፣ ጠንካራ ጥምረት እና መናበብ ነው።
ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልል ፖሊሶች፣ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከኢመደአ (INSA) የተዋቀረው የጋራ የፀጥታ እና ደኅንነት ግብረ-ኃይል ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥተዋል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ድብቅ ሴሎችን አስቀድሞ በማክሸፍ ሀገርን ከጥፋት ታድጓል።
በዲጂታሉ ግንባር ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የምርጫ ቦርድን "ምርጫዬ" መረጃ ቋት እና የቅሬታ መቀበያ መስመሮችን ከጥቃት በመጠበቅ የላቀ ሚና ተጫውቷል።
ተቋሙ በሀገር ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመለየት እና በማክሸፍም ለምርጫው እና ተያያዥ ሂደቶች መደላድል ፈጥሯል።
በተጨማሪም ሀገራዊ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ደኅንነታቸው የተጠበቁ ሀገር በቀል የመገናኛ መተግበሪያዎችን ወደ ሥራ አስገብቷል።
ተቋማዊ አቅም ለጠንካራ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ
ይህን ተቋማዊ ብቃት እና የፀጥታ ሥርዓት ፅናት ይበልጥ ዘላቂ እና ፍሬያማ ለማድረግ ሰፊ እና አካታች የሆነ ሀገራዊ የፖለቲካ ውይይት እና እርቅ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ሕዝቡ የተቋማት ገለልተኝነት ለሀገር ዘላቂ ጥንካሬ መሆኑን በመረዳት በእነዚህ ተቋማት ላይ የጋር አቋም ሊኖራቸው ይገባል።
የኢትዮጵያን ጠንካራ አስተዳደራዊ አቅም ከእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ጋር በማስተሣሠር ፅኑ፣ የተረጋጋች እና የበለጸገች ሀገርን መገንባት ይቻላል።
ለሚ ታደሰ