(የዕለቱ መልእክት)
ዲፕሎማሲ በዓለም አቀፍ መድረክ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነት እና ክብር ሳያስደፍሩ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚቀመር ረቂቅ የፖለቲካ ጥበብ ነው።
ዓለም በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ሽኩቻዎች በታመሰችበት በዚህ ዘመን የውጭ ግንኙነት መርሆዎችን እንደየአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እያስተካከሉ ጥቅምን ማስከበር የህልውና ጉዳይ ነው።
ባለፉት ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ምኅዳር ያጋጠሙትን ፈተናዎች የተሻገረው በዘፈቀደ ሳይሆን፣ "የውስጥ ጥንካሬ ለውጭ ዲፕሎማሲ ስኬት መሠረት ነው" የሚል ጽኑ እምነትን ሰንቆ ስልታዊና ጥልቀት ባለው የሪፎርም መነጽር በመመራቱ ነው።
በዚህም የተመዘገቡት ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ፈተናዎች አንጻር ሲመዘኑ እጅግ አስደማሚ ናቸው። እነዚህ ድሎች ሊመዘገቡ የቻሉት ቀደም ሲል የነበረውን በጥቂት ሀገራት ላይ ብቻ ያተኮረ የውጭ ፖሊሲ በመለወጥ፣ በአዲስ መልክ የተቀረጸ ገቢራዊ የሆነ የብዝኃነት ፖሊሲን በተግባር በመተርጎም ነው።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ (እንደ ቻይና እና ሩሲያ) እና በምዕራብ (እንደ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት) ኃይሎች መካከል በአንዱ ወገን ብቻ ሳትጠለል፣ ከሁሉም ጋር ያላትን ግንኙነት በማመጣጠን ብሔራዊ ጥቅሟን የማስከበር ስልታዊ ሚዛኗን ጠብቃለች። ይህንን ፖሊሲ ተከትሎ በተደረገ ከፍተኛ ጥረትም የስትራቴጂካዊ አማራጭ ስኬት የሆነውና በአንድ ወገን ፖለቲካዊ ጫና ውስጥ እንዳትወድቅ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዋስትና የሚሰጣት የብሪክስ ሙሉ አባል መሆን ተችሏል።
ከተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጋር የተሠራው ስኬታማ የሚዲያ ሥራና ሕዝባዊ ንቅናቄም የሀገርን ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ ከመገንባቱ ባለፈ፣ የሕዝብ ዲፕሎማሲ (Citizen Diplomacy) ምን ያህል አቅም እንዳለው ያሳየ ክስተት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጦርነትን የመከላከያ ጋሻ፣ ሰላምን የማስፈኛ ድልድይ እና የኢኮኖሚ ዕድገትን የማፋጠኛ ሞተር ሆኖ ያገለገለው በተለይ ከብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጋር በተያያዙ ትልልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ነው። ለአብነትም ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በስኬት ማጠናቀቅ የዲፕሎማሲያችን ትልቅ ድል ነው።
የዚህ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ሌላኛው አንጸባራቂ ስኬት፣ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያካሄደችው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ያገኘው ዕውቅና እና አክብሮት ነው። ምርጫው በዲፕሎማሲያዊ መድረክ የኢትዮጵያን የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብስለትና የፖለቲካ መረጋጋት በተግባር ያስመሰከረ ታላቅ ሁነት ሆኗል።
ምርጫው በሰላማዊና ሥልጣኔ በተሞላበት መንገድ መጠናቀቁ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋር ሀገራት ለኢትዮጵያ የውስጥ ጥንካሬና ሉዓላዊ ምርጫ ያላቸውን አመለካከት በአዎንታዊ መልኩ እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል። ይህም የሀገራችንን የዲፕሎማሲ የሞራል የበላይነት ከፍ ከማድረጉም በላይ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ስኬት አስተማማኝ መሠረት ጥሏል።
ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የመስጠት ፖሊሲ እና የባሕር በር ለማግኘት የተጀመሩት ስትራቴጂካዊ ጥረቶችም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የመሪነት ሚና ይበልጥ አድምቀውታል።
ይሁንና የወደፊቱ የዲፕሎማሲ ስኬታችን ቀጣይነት እንዲኖረው የውጭ ፖሊሲያችን ይበልጥ በብሔራዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ፣ በዕውቀት የሚመራ እና ጠንካራ የውስጥ ሰላምን መሠረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል። የተጀመረውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ይህ በጽናትና በብልሃት የተገኘው የዲፕሎማሲ ስኬት ሁልጊዜም የንቃትና የጥንካሬ መገለጫችን ሆኖ ሊቀጥል ይገባል።
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል መልእክት