Search

ኢትዮጵያ በኒው ዴልሂ እየተካሄደ ባለው 11ኛው የብሪክስ የውጭ ፖሊሲ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው

እሑድ ግንቦት 30, 2018 68

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስትራቴጂያዊ ዕቅድ እና ክትትል ዋና ዳይሬክተር መኮንን ጎሳዬ የተመራ ኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሕንድ አስተናጋጅነት በኒው ዴልሂ እየተካሄደ ባለው 11ኛው የብሪክስ የውጭ ፖሊሲ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

ይህ የብሪክስ አባል ሀገራት ከፍተኛ የውጭ ፖሊሲ እና የዕቅድ ባለሥልጣናትን እንዲሁም ባለሙያዎችን ያገናኘው የውይይት መድረክ ፈጠራ፣ ትብብር እና ዘላቂነት ባሉ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ የሐሳብ ልውውጥ የተደረገበት ነው።

ጉባኤው ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ግንኙነት እና ለተጠናከረ የደቡብ-ደቡብ ትብብር ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠችበት ሆኗል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ዳይሬክተር መኮንን ጎሳዬ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት እርምጃ ያላትን ቁርጠኝነት አብራርተዋል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሣሽነት የተጀመረውን እና ሥነ-ምኅዳርን ለመመለስ እና የአካባቢ ዘላቂነትን ለማስቀጠል ሀገር አቀፍ ጥረቶችን ማንቀሳቀስ የቻለውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብርን በምሳሌነት ለአባል ሀገራቱ አቅርበዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ አካታች ዕድገት እና ልማትን ለማምጣት ሰፊ ራዕይ የሆኑትን እና በኢኮኖሚ እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ረገድ እያሳየች ያለችውን ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማብራራታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ይህም በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ፣ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ መፍትሔዎች እና በኤሌክትሮኒክ-አስተዳደር አገልግሎቶች ላይ የታዩ ስኬታማ ማሻሻያዎችን ያጠቃልላል።

ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያላትን ዝግጁነት የገለጸች ሲሆን ዘላቂ ልማትን እና የጋራ ብልጽግናን ለማስመዝገብ የጋራ እውቀት፣ አረንጓዴ ፋይናንስ እና የጋራ አቅም ወሳኝ ምሰሶዎች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥታለች።

በሀና ምንዳሁን