በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት “አረንጓዴ እና ጽዱ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ በግንባር ቀደምትነት የሚያስጠራት ታላቅ ስኬት አስመዝግቧል።
ጅማሮው በአንድ ቀን ውስጥ 350 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለም የክብረ ወሰን ታሪክ የተጻፈበት ሲሆን፣ ብሔራዊ ንቅናቄው አሁን ላይ ችግኝ ከመትከል ተሻግሮ ባዶ መሬቶችን ወደ ምርታማ የፍራፍሬ እና የሰብል ማዕከላት በመቀየር የምግብ ዋስትናን በተግባር የማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ አንዱ ስኬት ቀደም ሲል በአፈር መሸርሸር እና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ብርቱካን ያሉ ፍራፍሬዎች ወደሚመረቱባቸው ስፍራዎች መለወጡ ነው።
ይህ ስትራቴጂያዊ ለውጥ የአካባቢውን ሥነ-ምኅዳር ከመመለሱ ባሻገር፣ አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ቀጥተኛ የምግብ ምንጭ እና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ የዜጎችን የኑሮ አቅም አሳድጓል።
መርሐ ግብሩ የአፈርን እርጥበት የመጠበቅ፣ የከርሰ ምድር ውኃን የመሙላት እና መሸርሸርን የመከላከል አቅምን በማሳደግ ለሰብል ምርት ዕድገት የላቀ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በዚህም መነሻነት ቀደም ሲል ለድርቅ ይጋለጡ የነበሩ አያሌ መሬቶች ዛሬ ላይ በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ በሰብል እንዲሸፈኑ አስችሏል። ይህም እንደ ስንዴ፣ በቆሎ እና ጥራጥሬ ያሉ ሰብሎች በበቂ ሁኔታ እንዲመረቱ በማድረግ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ለመተካት እና ለማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና በተሻሻሉ የግብርና ስትራቴጂዎች አማካኝነት፣ ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ኤክስፖርት ማድረግ የቻለች ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያ ከነበረባት የምግብ ዕርዳታ ተላቃ ራሷን እንድትችል እና ለሌሎች ሀገራት አርአያ እንድትሆን አድርጓታል።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት (FAO) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ«ፋኦ አግሪኮላ ሜዳሊያ» (FAO Agricola Medal) ማበርከቱ ይታወሳል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት መዛባትን እና በረሃማነትን እየተከላከለ የኢትዮጵያን ዘላቂ የምግብ ዋስትና በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
በሀና ምንዳሁን