የአማራ ክልል "ኢትዮጵያ ታምርት" የንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ ክልሉን ተወዳዳሪ እና ቀዳሚ ለማድረግ ሁሉም አካል በቅንጅት እና በትብብር ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በራስ አቅም የማደግ፣ የራስን ምርት የማሳደግ እና የመጠቀም እንዲሁም ሀገርን በአንድነት የማበልጸግ እሳቤ የወለደው መሆኑን አቶ አረጋ ገልጸዋል።
"ሀገር የተሟላ ሉዓላዊነት እና ነፃነት የሚኖራት በሁሉም መስክ ራስን መቻል ሲቻል ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በምርት ራሱን ያልቻለ ሀገር የሌሎች ሀገራት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጥገኛ መሆኑ እንደማይቀር አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በቀኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር ብትሆንም፣ የተሟላ ነፃነት እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ሕዝቡን ከድህነት እና ኋላቀርነት ማላቀቅ እንዲሁም በምርት ራስን መቻል የውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አብራርተዋል።
የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረው መምጣቱን ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ የኃይል፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና ሌሎች ማነቆዎች በሂደት እየተፈቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የማምረት አቅም ከበፊቱ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ጠቁመው፣ አሁንም ግን ለአነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪ በፀጥታ ችግር ውስጥ ማለፉን በማስታወስም፣ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ራሱ የፀጥታ ችግሩን እንደሚፈታው ተናግረዋል።
"ኢኮኖሚው ያደገ ሀገር እና ሕዝብ ወደ ግጭት አይገባም" በማለትም የኢንዱስትሪው ዕድገት ለሰላም ያለውን አስተዋፅኦ አጉልተዋል።
ይህንንም መሠረት በማድረግ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የክልሉ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ መደረጉን ገልጸዋል።
የፀጥታ ችግር ሳይበግራቸው በክልሉ በመሥራት ለውጤት የበቁ ባለሀብቶችን አመስግነዋል።
"የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የክልሉን ጸጋ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሀብቶች ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትሥሥር ለመፍጠር እና የመንግሥት እና የባለሀብቱን ቅርርብ ለማሻሻል ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።
የክልሉ መንግሥት አዳዲስም ሆነ ነባር ባለሀብቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ሌሎች ባለሀብቶችም ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።