Search

አረንጓዴ ዐሻራ - የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዲስ ሞተር

እሑድ ግንቦት 30, 2018 60

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሥነ ምኅዳር ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያነትን ተሻግሮ፣ የሀገራችን ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት መሪ ሞተር እና አዲሱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እየሆነ መጥቷል።

ከተፈጥሮ ጥበቃው ባሻገር ያለው ተጨባጭ የኢኮኖሚ እምቅ አቅም በሀገራችን ቁልፍ ዘርፎች እና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ ትልቅ መዋቅራዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

ይህ ታላቅ ብሔራዊ ንቅናቄ በሁለት ምዕራፎች 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበሱን ቀጥሏል።

ይህ ተግባር የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማቋቋም የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ እና የብዝኃ ሕይወትን በመጠበቅ ረገድ ዓለም አቀፍ አድናቆትን ከማትረፉም በላይ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ መድረክ የድርድር አቅሟን እንድታሳድግ አስችሏታል።

በግብርና ምርታማነት እና የምግብ ዋስትና ላይ የደን ሽፋኑ መጨመር የአፈር መሸርሸርን በመግታት የከርሰ-ምድር ውኃ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲበለጽግ አድርጓል።

ይህ የተፈጥሮ ሚዛን መስተካከል የግብርና ምርታማነትን ከማሳደጉም በላይ፣ የሀገራችንን የክረምት ዝናብ ጥገኝነት በመቀነስ ለዘመናዊ የመስኖ ልማት እና ለበጋ ስንዴ ምርት ሰፊ እና አዳዲስ ምቹ ዕድሎችን ከፍቷል።

በተለይም አቮካዶ፣ ፓፓያ እና አፕልን ጨምሮ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት መተከላቸው የሀገር ውስጥ ገበያን ከማረጋጋት አልፎ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ጠንካራ ግብዓት በመሆን እና በውጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ዘርፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ላይ ይገኛል።

ይህ ንቅናቄ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን፣ በተለይም ሴቶችን እና ወጣቶችን በችግኝ ማፍላት እና መትከል ሂደቶች ላይ በማሳተፍ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

ከዚህም ባለፈ የአካባቢ መለምለም እንደ ዘመናዊ የንብ ማነብ፣ የፍራፍሬ ልማት እና የሐር ምርት ያሉ አዳዲስ እና ዘላቂ የገቢ ምንጮችን ለአርሶ አደሩ እና ለአነስተኛ ነጋዴዎች በማስገኘት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን አጠናክሮታል።

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የጀመረችውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ የአረንጓዴ ዐሻራ ሚና የላቀ ነው።

በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ እንዲሁም በሌሎች የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ተፋሰስ አካባቢዎች የሚደረገው የችግኝ ተከላ የአፈር ደለል ወደ ግድቦቹ እንዳይገባ ይከላከላል።

ይህም የኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን ደኅንነት በመጠበቅ የግድቦቹን ዕድሜ እና የማመንጨት አቅም ያሳድጋል።

የኢትዮጵያ ደኖች እያደጉ ሲሄዱ የሚመጥጡትን የካርቦን መጠን ወደ ገንዘብ በመቀየር ወደ ዓለም አቀፉ የካርቦን ገበያ እና እንደ REDD+ ወዳሉ የካርቦን ንግድ ሥርዓቶች ለመግባት ሰፊ በር ከፍቷል።

ይህም ሀገራችን አዲስ የውጭ ምንዛሬ እና የአረንጓዴ ልማት ፈንድ እንድታገኝ ያደርጋታል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን በማጋራት የምታሳየው አረንጓዴ ዲፕሎማሲ በቀጣናው የትብብር መንፈስን በመፍጠር፣ የበረሃማነት መስፋፋትን በጋራ ለመከላከል እና የጋራ የባሕር ዳርቻ እና የወደብ ደኅንነትን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትሥሥርን ለማጠናከር ትልቅ መሣሪያ ሆኗል።

በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት እያገገሙ የመጡ የተፈጥሮ ደኖች እና በመዲናዋም ሆነ በክልሎች የተገነቡት ዘመናዊ አረንጓዴ ፓርኮች ለቱሪዝም ዘርፉ አዲስ ሕይወት ዘርተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የምትመኘውን ዘላቂ፣ ሁሉን አቀፍ እና ለአየር ንብረት የማይበገር ዘመናዊ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ሥርዓት ለመገንባት ዋነኛ ስትራቴጂያዊ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በሔዋን ጌታቸው