7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በስኬት የተካሄደና የሰከነ የፖለቲካ ፉክክር የታየበት መሆኑን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ገለጸ።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሁ እንደገለጹት፤ የዘንድሮው ምርጫ ሂደት ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አንጻር በጥሩ ሁኔታ የተከናወነና ስኬታማ ነበር።
አቶ መስዑድ እንዳሉት፣ በዘንድሮው ምርጫ ዜጎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል።
በምርጫው የፉክክር ሂደት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ ሃሳባቸውን ለህዝብ ሲያቀርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ የነበራቸው መናበብ አስደማሚ እንደነበር መታዘባቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ይህም ፖለቲካ ፓርቲዎች የባሕር በር ባለቤትነትን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅሞች መከበር የሰከነ የፖለቲካ ምኅዳር በመፍጠር እየተሳተፉ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ አክለዋል።
በምርጫው ወቅት የተስተዋለው የምርጫ ጣቢያዎች አሠራርም ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ዜጎችን የመምረጥ መብት ያረጋገጠ ነበር ብለዋል።
በተለይ ለአካል ጉዳተኞች፣ መስማት ለተሳናቸው፣ ለነፍሰ ጡሮችና ጨቅላ ሕፃናት ለያዙ ወላጆች ምቹ ምኅዳር ተፈጥሮ እንደነበር በአብነት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።