የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች ኢማኑኤል ኢቦኤ በአዲስ አበባ ውበት መደነቁን ገለፀ።
አዲስ አበባ ውብ ናት ያለው ኢማኑኤል ኢቦኤ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ተናግሯል።
አርሰናል የ2026 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ በአዲስ አበባ የደስታ መግለጫ ዝግጅት መካሄዱ ይታወቃል።
በዝግጅቱ ተካፋይ ለመሆን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ኢማኑኤል ኢቦኤ እና የኤኤፍ ቲቪ (የአርሰናል ደጋፊዎች ቴሌቪዥን) አባላት በአዲስ አበባ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
እንግዶቹ አዲስ ስፖርት ፓርክን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን በዚህም መደነቃቸውን ገልጸዋል።
ኢማኑኤል ኢቦኤ በአዲስ አበባ በተመለከተው ዘመናዊነት ስለመደነቁ መናገሩን ኤኤምኤን ዘግቧል።
ጎብኚዎቹ፣ የከተማዋ አረንጓዴነት፣ ጽዳት እና አጠቃላይ ውበት እጅጉን ማራኪ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ምቹ የአየር ንብረት፣ በነዋሪዎቿ እንግዳ ተቀባይነት እንዲሁም በከተማዋ ዘመናዊነትና ፈጣን ዕድገት እንደተደነቁ ተናግረዋል።
ይህም ከተማዋ በውጭ ቱሪስቶች ያላትን ተመራጭነት ይበልጥ እንደሚያሳድገው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።