በሀገራችን በስኬት የተከናወነው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝባችንን የካበተ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ንቃተ-ሕሊና እና የነገዋን ሀገር በጋራ የመሥራት ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ ሆኗል።
ምርጫው ዜጎች ድምፃቸውን ከመስጠት ባለፈ ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ መንገድ በማስተናገድ የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና የውስጥ አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ያላቸውን መሻት ለዓለም ያሳዩበት ጭምር ነው።
በምርጫው ዕለት የተስተዋለው የኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ሕዝቡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ታማኝነት በግልጽ ያሳየ ነበር።
ገና በማለዳው በየምርጫ ጣቢያቸው ተገኝተው ረጃጅም ሰልፎችን በትዕግሥት በመቋቋም ድምፃቸውን የሰጡት እናቶች፣ አባቶች እና ወጣቶች ያሳዩት ጽናት የምርጫውን ታሪካዊነት ይበልጥ አጉልቶታል።
ይህም በኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ዘላቂ የፖለቲካ ባህልን ለመገንባት ሕዝቡ ግንባር ቀደም ባለቤት መሆኑን ያረጋገጠ ክንውን ነው።
ከሁሉ በላይ ደግሞ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያውያንን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ ያጠናከረ ሆኗል።
ከተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና እምነቶች የተውጣጣው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት መንፈስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በማምራት በጋራ ዕጣ ፈንታው ላይ በየግሉ በነፃነት ወስኗል።
ይህ ታላቅ ሀገራዊ ትዕይንት ልዩነቶች የውበት እንጂ የጥርጣሬ ምንጭ ሊሆኑ እንደማይችሉ እና በፈተናዎች ውስጥም ሀገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጠ ሁነት ነው።
በጥቅሉ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና የሕዝቦችን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ ያጸና ታሪካዊ ክንውን ሆኖ ይጠቀሳል።
ሕዝባዊ አንድነት ጎልቶ የታየበት ዴሞክራሲያዊው የምርጫ ሂደት፣ ኢትዮጵያውያን በኅበረት አሸናፊ የሆኑበት እና የሀራችንን የነገ ብሩህ ተስፋ ያመላከተ ነው።
የተገኘው ስኬትም ለቀጣይ ሀገራዊ ልማት እና ግንባታ ሰፊ እና አስተማማኝ ሕዝባዊ መሠረት እንደሚያደላድል ይጠበቃል።
በሔዋን ጌታቸው