ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከ130 ሚሊዮን በላይ የሚሆን እጅግ ሰፊ ሕዝብ ይዛ የባሕር በር አልባ ሆና እንድትቀጥል የተፈረደባት ብቸኛ ሀገር ናት።
ይህ ታሪካዊ ኢ-ፍትሐዊነት ትውልዱ ላይ ጥልቅ ቁጭት እና የሕልውና ጥያቄ የፈጠረ እና ምላሽ የሚሻ ነው።
ከቅድመ አክሱም ዘመን ጀምሮ እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን እና ቀይ ባሕር ተነጣጥለው አያውቁም።
ከ1985 ዓ.ም እስከ 'መደመር ትውልድ' መነሣት ድረስ ያለው ትውልድ ግን በታሪክ "የሥነ-ልቦና ስብራት" ዘመን ተብሎ የሚታወቅበትን የባዶነት እና የቁጭት ጊዜ አሳልፏል።
በወቅቱ ሥልጣንን የተቆጣጠሩት ኃይሎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተመሳጥረው ታሪኩን የነጠቁት ያ ትውልድ፣ የባሕር በር ማጣትን እንደማይቀየር ቋሚ ዕጣ ፈንታ በመቁጠር ሲብሰለሰል ኖሯል።
ከ12 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ የሚተላለፍበትን እና በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን ቀይ ባሕርን ዝም ብሎ ማየት ያንገፈገፈው "የመደመር ትውልድ" ዛሬ ተፈጥሯል።
የመደመር ትውልድ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን አምራች እና ወጣት ሕዝብ የሚወክለው የቀይ ባሕር ትውልድ ነው።

ይህ ትውልድ የባሕር በር አልባነትን እንደ ቋሚ ዕጣ ፈንታ ሳይሆን እንደ ታሪካዊ እና ሕጋዊ ስህተት ይመለከተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንደገለጹት፣ በ2050 ዓ.ም የሕዝብ ብዛቷ ወደ 150 ሚሊዮን ተብሎ የምትገመተዋ ታላቅ ሀገር መተንፈሻ አልባ ሆና መቀጠል አትችልም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው እንደገለጹት ይህን ያህል ግዙፍ ሕዝብ ያላትን ሀገር በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ውስጥ አስገብቶ ለቀጣዩ ትውልድ ማውረስ የታሪክ ባለእዳነት ነው።
የቀይ ባሕር ትውልድ ታሪክን የማረም እና የታላቋን ኢትዮጵያን ትክክለኛ የጂኦግራፊ እና የኢኮኖሚ ስፍራ የመመለስ ታሪካዊ አደራ ወድቆበታል።

ይህ ትውልድ የባሕር በር ጥያቄ የፖለቲካ ቅንጦት ሳይሆን፣ የ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሕልውና እና የዕድገት መሠረት መሆኑን በሚገባ የተገነዘበ ጠንካራ ሥነ-ልቦና አለው።
የቀይ ባሕር ትውልድ ታሪካዊ ስህተቶችን ለማረም የሚንቀሳቀሰው በጦርነት አዙሪት ሳይሆን፣ በጋራ ተጠቃሚነት፣ በኢኮኖሚያዊ ውህደት እና በብልህ የፓን-አፍሪካኒዝም ዲፕሎማሲ ነው።
ትውልዱ ኢትዮጵያ የምትገነባቸውን ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ጋር በማስተሳሰር፣ ቀጣናውን የጋራ ብልጽግና ማዕከል ለማድረግ ይተጋል።
በለሚ ታደሰ