Search

ኢቢሲ በራሱ አቅም ዲጂታል ሆኗል፦ የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌትነት ታደሰ

ረቡዕ ነሐሴ 07, 2017 163

ኢቢሲ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደራሽ እና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድምፅ ለመሆን በርካታ ሥራዎች እየከወነ መሆኑን የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ገለጹ። 

ዋና ሥራ አስፈፃሚው የኢትዮጵያ ድምፅ ከሀገር አልፎ በአህጉር ደረጃ ተደማጭ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን አንሥተው፣ ኢቢሲ ያሉትን ሁሉንም የይዘት አማራጮች በዲጂታል መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። 

በተለይም ኢቢሲ ዛሬ ካስመረቃቸው ሥርዓቶች ውስጥ ሁሉንም የይዘት አማራጮቹን ከዶትስትሪም የማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ጋር አንድ ላይ የሚገኝበት የሞባይል መተግበሪያ የኢቢሲን ዲጂታል መንገድ የሚያሳድግም መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በተጨማሪም የኢቢሲ ድረ ገጽ እና የኢቢሲ ውስጣዊ የዲጂታል ሥራ ማስኬጃ ሥርዓት "እርሳስ"ን ጨምሮ ተቋሙን በዲጂታል ኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የሚያገዝፉ ከ25 በላይ መተግበሪያዎች እና ሥርዓቶች በመሠራታቸው ወደ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች የተሸጋገርንባቸው ሆነዋል ብለዋል። 

ከዚህ በፊት ለረጅም ጊዜ በነበረን አሠራር ከመሐል ሆኖ ወደ ዳር የመዘገብ ልምምድ የዳር እና የመሐል ጨዋታ ነበረ ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሁን ይህን ለመቀየር ተጨባጭ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

ለዚህም በስምንት ክልሎች የይዘት ምንጭ የሚሆኑ ስቱዲዮዎችን በማስፋት የቆየውን “የዳር የመሐል” ትርክት በተግባር መቀየር ተችሏል ብለዋል። 

ይህን እውን ያደረግነው በውስጥ አቅም ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የተቋሙን የዲጂታል ጉዞ ዕውን ለማድረግ በትጋት እና በሞያዊ ሥነ ምግባር ለሠሩ ባለሙያዎች ምስጋናም አቅርበዋል። 

ከዚህ ባለፈ ተቋሙ ወደ ዲጂታል ባደረገው ጉዞ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ሌሎች ተቋማትም ከኢቢሲ ጎን ቆመው ላደረጉት ሞያዊ ድጋፍ እና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አትሌቶች፣ አርቲስቶች፣ የተቋሙ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

በሰለሞን ከበደ