Search

የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ቴክኖሎጂዎችን በራስ አቅም ማልማትና መጠቀም ይገባል - አቶ ቢኒያም ማስረሻ

ረቡዕ ነሐሴ 07, 2017 114

በዲጂታል ዓለም ውስጥ በአርበኝነት ስሜት የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ፣ ቴክኖሎጂዎችን በራስ አቅም በማልማትና በማበልጸግ መጠቀም ይኖርብናል ሲሉ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህልና ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ቢኒያም ማስረሻ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ (አፕ) በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ "ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የዲጂታል ሚዲያው ሚና ምንድን ነው" በሚል በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ አቶ ቢኒያም ማስረሻ የመነሻ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡

አቶ ቢኒያም ማስረሻ በዚሁ ወቅት፤ አሁን ባለው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ቴክኖሎጂን መጠቀም ብቻ ሳይሆን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዲጂታል ዓለም ውስጥ ሆነን የዲጂታል ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ካልተቻለ ለጥቃት ተገላጭነታችን እየሰፋ ይሄዳልም ነው ያሉት፡፡

ቴክኖሎጂን በራሳችን አቅም ማልማትና መጠቀም እስካልቻልን ድረስ ጥገኛ እንሆናለን ያሉት አቶ ቢኒያም፤ የዲጂታል ጥገኝነት እስካለብን ድረስ የሉዓላዊነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አሁን ያለው ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመረጃ ጦርነት የሚካሄደበት ዘመን ነው ያሉት አቶ ቢኒያም፤ የህዳሴው ግድብ ጨምሮ ከምርጫ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲጂታል መረጃ ጦርነት የሚካሄደበት ወቅት ላይ ነን ብለዋል፡፡

በመሆኑም በዲጂታል አርበኝነት ዙሪያ ሁሉንም ተቋማትና ግለሰቦች ለማብቃት ካልተሰራ  ከፍተኛ ፈተና ይገጥመናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሳይበር ደህንነትን ጥቃትን ለመከላከል አንድ ተቋም ቴክኖሎጂውን የሚያስተዳድርበት የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ፣ አደረጃጀት፣ መሰረተ ልማቱን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ ረገድ ያለበት ደረጃ፣ የሰለጠና ባለሙያ፣ የንቃተ ህሊና ፕሮግራም አለ ወይ የሚለው መፈተሽ አለበት ሲሉም ዓለም አቀፍ ስታንደርድ የሚጠይቀውን መስፈርት አብራርተዋል፡፡

በአምስቱም የዝግጁነት ደረጃ ላይ ሲታይ የሚዲያው ዘርፍ ከሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ያለው ዝግጁነት በዝቅተኛ ደረጃ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሚዲያው ዘርፍ የሚደርሰውን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ደረጃ የገለጹት አቶ ቢኒያም፤ በአጠቃላይ 57.3 በመቶ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ነን ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የተጋላጭነት ደረጃችን ከፍተኛ ስራ መስራት እንዳለብን ያመለክታል ያሉት አቶ ቢኒያም፤ 49 በመቶ ያህል ደግሞ የሳይበር ጥቃት ስጋት ተመዝግቦ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመሀመድ ፊጣሞ

#EBC #ebcdotstream #Digital_EBC #DigitalEthiopia #EBCApp