ኢቢሲ ያለውን የመረጃ ሀብት በሰውሰራሽ አስተውሎት ዘመን ካለው የመረጃ ክምችት ጋር በማስተሳስር ትልቅ ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ (አፕ) በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ "ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የዲጂታል ሚዲያው ሚና ምንድን ነው" በሚል በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) የመናሻ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው፤ መረጃ ለሚዲያ ዘርፍ ካስማ መሆኑን ገልፀው፤ ይህንንም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ተወዳዳሪ እና ቀዳሚ ሆኖ ለመጠቀም እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡
ተመልካች እና አድማጭ የተለያየ የመረጃ ፍላጎት እንዳለው በማስታወስ በራስ አቅም የበለፀገው የኢቢሲ መተግበሪያ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በተመልካች የመረጃ ፍላጎት መሰረት መረጃን ማቀበል የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም መረጃን በተለያየ ቋንቋ ለማቅረብ የሚያግዝ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሥራ እድል ያሳጣል እና መሰል በሆኑ ሃሳቦች እንደ ችግር ከማየት ይልቅ እራስን ከተለዋዋጩ ዓለም ጋር እኩል ማስኬድ እና ዝግጁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ኢቢሲም ዘመኑ ያመጣውን እድል በመጠቀም ሰራተኞችን ማብቃት እና ማሳወቅ ላይ የሰራውን ስራ አድንቀዋል፡፡
በአፎምያ ክበበው
#EBC #ebcdotstream #Digital_EBC #DigitalEthiopia #EBCApp