የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ስብሰባው የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት ረቂቅ አዋጅን አስመለክቶ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ በሙሉ አፅድቋል።
ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ዘርፉ ከሚመለከታቸው የመንግሥት እና የግል ተቋማት ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን እና የተለዩ ጭብጦችን አብራርተዋል።
የሳይበር ደኅንነት ፕሮግራሞችን ለማስፈጸም፣ ለሥልጠና፣ ለምርምር እና ለቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ የሚውል ራሱን የቻለ የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት ፈንድ በአዲስ ምዕራፍ መደንገጉንም አስረድተዋል።
በአዋጁ አፈጻጸም እና በቅጣት አወሳሰድ ላይ በመንግሥት እና በግል ተቋማት መካከል የነበረው ልዩነት ተሰርዞ አዋጁ በመንግሥትም ሆነ በግል ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ እኩልና ፍትሐዊ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ተደርጓልም ብለዋል።
ማንኛውም የመሠረተ ልማት ባለቤት፣ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ሆን ብሎ ጥፋት ካጠፋ በሕግ ይጠየቃል ያሉት ዶክተር ዲማ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ወቅታዊ የደኅንነት ሁኔታዎችን እና የሳይበር ጥቃት ስጋቶችን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል ብለዋል።
ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ለሀገር ሰላም እና ሉዓላዊነት ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው የተረዳው ምክር ቤቱ፤ በቋሚ ኮሚቴው በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1426/2018 አድርጎ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።