ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት 10 ወራት ከወጪ ንግድ የ8.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
ይህ ገቢ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ38.9 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ጫናዎችን በመቋቋም የተገኘው ገቢ 8.7 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅ 10.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚመዘገብ መገመቱን በዛሬው ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የበጀት መግለጫ ገልጸዋል።
እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት 10 ወራት ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባቻቸው የገቢ ንግድ 18.4 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህም ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ17.9 በመቶ ዕድገት እንዳለው ተናግረዋል።
የፌዴራል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ውሳኔ ቁጥር 24/2018 ሆኖ ለፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።