Search

በሦስት የተለያዩ ከተሞች በሚካሄዱ ሥነ-ሥርዓቶች የሚከፈተው ዓለም ዋንጫ

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 143

23ኛው የዓለም ዋንጫ ከሰዓታት በኋላ ሲጀመር በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የመክፈቻ ዝግጅት እንደሚኖረው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማኅበር(ፊፋ) አስታውቋል።

ዓለም ዋንጫውን በጣምራ የሚያስተናግዱት ሀገራት የተለያየ የመስተንግዶ አላቸው። አሜሪካ ለሁለተኛ ጊዜ፣ ሜክሲኮ ለሦስተኛ ጊዜ እንዲሁም ካናዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የዓለም ዋንጫን የሚያዘጋጁት።

በሦስት ከተሞች የሚካሄዱት የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቶች እርስ በእርስ የተሳሰሩ ሲሆኑ፣ ዛሬ ሜክሲኮ ደቡብ አፍሪካን ከምትገጥምበት የመክፈቻ ጨዋታ ዘጠና ደቂቃ ቀድመው ይጀምራሉ።

በሦስቱም ከተሞች የተዘጋጁት የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቶች የሚጋሩት ይዘት ኖሯቸው ባህልን፣ ታሪካዊ ማንነትን እና ፈጠራን እንዲያንፀባርቁ ይደረጋል ተብሏል።

የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ አዘጋጅ ማርኮ ባሊች ይሰኛል። ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ኦሎምፒክን ጨምሮ የበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቶች እንዳዘጋጀ ተነግሯል።

የየከተሞቹ ዝግጅቶች የተለያዩ መገለጫዎች ይኑራቸው እንጂ፣ ያለ ድንበር ሕዝቦችን በሚያዋህደው እግር ኳሳዊ ቋንቋ መሰረት ላይ ይተሳሰራሉ።

ሁሉም ሀገር ይገልፀዋል የተባለ የጥበብ ሥራ በመክፈቻ ሥነ-ሥርዐዓቶቹ ላይ ይንፀባረቃል። ካናዳ በባህላዊ የሞዛይክ ጥበብ ስትወከል፣ ሜክሲኮ ፔፐል ፒካዶ በተሰኘ ኅብረ ቀለማዊ ትዕይንት ራሷን ትገልፃለች ተብሎ ይጠበቃል።

አሜሪካም በተለመዱት የጥበብ ሥራዎች መክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደምትታይ አዘጋጁ ማርኮ ባሊች ተናግሯል።

ጣሊያናዊው አዘጋጅ ማርኮ ባሊች የእግር ኳስን መልክ ከሀገራቱ ባህል ጋር የሚያስተሳስር ሥነ-ሥርዓት አዘጋጅተናል ብሏል።

መክፈቻው ከዛሬው ጨዋታ በፊት ጀምሮ ነገ ካናዳ ቦስኒያ ሄርዞጎቪኒያን ከምትገጥምበት ጨዋታ በፊት ቶሮንቶ ላይ እንዲሁም ከነገ በስቲያ አሜሪካ ፓራጓይ ከምትጫወትበት ጨዋታ አስቀድሞ ሎስ አንጀለስ ላይ የሚቀጥል ይሆናል።

የተለያዩ ማንነትን፣ ባህልን፣ የዘመናት ውጣ ውረድን ከሚገልፁ ትዕይንቶች ጎን በእውቅ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሚቀርቡት ዝግጅቶችም ሌሎቹ ዐበይት የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቶቹ አካላት ናቸው።

ወቅቱ ደርሶ 48 ሀገራት የሚሳተፉበት፣ በሦስት ሀገራት የተሰናዳው ታሪካዊው የዓለም ዋንጫ ሊጀመር ሰዓታት ቀርተዋል።

በእድሪስ አህመድ